ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን ውስጥ በጎርፍ ሳብያ ከ50 በላይ ሲሞቱ በርካቶች ላይ ጉዳት ደረሰ
የክረምቱ ወቅት ከጀመረ በኋላ ባለው ጊዜ ሱዳን ውስጥ ከ50 በላይ ሰዎች በከባድ ዝናብና ጎርፍ ሳብያ ሕይወታቸው መጥፋቱን መንግሥትና የእርዳታ ተቋማት አሳወቁ።
ካለፈው ግንቦት ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ በተከሰተው ጎርፍና ከባድ ዝናብ የተነሳ 136 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ለችግር የተዳረጉ መሆናቸውንና በርካታ ሰዎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል ሲል የሱዳን መንግሥት የሰብአዊ እርዳታ ኮሚሽን ገልጿል።
ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ያመለከተው ኮሚሽኑ፣ በዚህም ባለፉት ወራት ውስጥ 52 ሰዎች ሲሞቱ 25 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በተጨማሪም ጎርፉ በ12 የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ 8,900 የሚሆኑ ያወደመ ሲሆን በሌሎች 20,600 ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።
በጎርፍ ጉዳት ከደረሰባቸው ግዛቶች መካከል ከፍተኛው ሞት የተመዘገበው በሰሜን ኮርዶፋን 19 ሰዎች ሞተዋል።
በተከታይነት ደግሞ በናይል ሪቨር ግዛት ውስጥ ደግሞ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን የሱዳን ብሔራዊ የሲቪል መከላከያ ምክር ቤት ቃል አቀባይ የሆኑትን ብርጋዲየር ጄኔራል አብዱል ጃሊል አብዱል ራሁምን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና ወኪል ዘግቧል።
ከመንግሥት ኮሚሽን እና ከእርዳታ ድርጅቶች የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በጎርፉ እና በከባድ ዝናብ ሳብያ በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ መጠናቸው ከ130 ሺህ በላይ ሰዎች ለችግር ተጋልጠዋል። ከእነዚህም መካከል የማዕከላዊ ዳርፉር፣ደቡብ ዳርፉር፣ ናይል ሪቨር እና ዋይት ናይል ከሌሎቹ በላቀ በርካታ ሕዝብ ችግር ገጥሞታል።
ጎርፉ በሰው ላይ ካስከተለው ጉዳት ባሻገር በርካታ የጤና ተቋማት፣ የውሃ እና የንጽህና መሠረተ ልማቶችን ማውደሙ ተገልጿል።
በተጨማሪም በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶች በጎርፉ ሲወሰዱ፣ ወደ 20 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የእርሻ መሬት ጉዳት ደርሶበታል።
የሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ዕቅድ እንዳመለከተው በየዓመቱ በርካታ ሕዝብ በጎርፍ ሳብያ ጉዳት እየደረሰበት ቢቆይም በአሁኑ ዓመት የተከሰተው ይህ ጉዳት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው።
በሱዳን ውስጥ የአባይ ወንዝ መጠን ካለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ አንስቶ እየጨመረ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ነገር ግን ስጋት ከሚሆንበት ደረጃ ላይ አልደረሰም ተብሏል።
የአትባራ ወንዝም እንዲሁ በኢትዮጵያ በኩል እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ከስጋት ደረጃው ከፍ ማለቱን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
በጎርፍ በተጥለቀለቁት የሱዳን ግዛቶች ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች እርዳታ ለማድረስ አመቺ የሆኑ ቦታዎችን ለመለየት ፈጣን የሁኔታዎች ግምገማ በረድኤት ድርጅቶች እየተደረገ ነው።
በሱዳን የዝናብ ወቅት በአብዛኛው የሚጀምረው በሰኔ ወር ላይ ሲሆን አስከ መስከረም ወር ድረስ የሚቀጥል ይሆናል።