ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤልና ሐማስ ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ እንዲገባ ስምምነት ላይ ደረሱ
እስራኤልና ሐማስ በሰብዓዊ አቅርቦት ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አደራዳሪዋ ኳታር አስታወቀች።
ስምምነቱ ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ በሚገባበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
ከኳታር ሌላ በማደራደሩ ሂደት ፈረንሳይ ተሳትፎ እንዳላት ተነግሯል።
በዚህ ስምምነት መሠረት በሐማስ ለተያዙ ታጋቾች አስፈላጊ መድኃኒት እንዲደርስ መግባባት ላይ ተደርሷል።
እስራኤል በምላሹ ደግሞ አስፈላጊ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ትፈቅዳለች።
ላለፉት ሦስት ወራት ያለማቋረጥ በቦምብ ጥቃት ሲፈጸምባት በቆየችው ጋዛ አሁን ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ የሚባል ነው።
አሜሪካ ድርድሩ ተጠናክሮ ቀጥሎ ታጋቾች የሚለቀቁበት ሁኔታ ይኖራል የሚል ተስፋ አለኝ ብላለች።
የአሜሪካ ልዩ ልኡክ ይህን ለማሳካት ወደ ኳታር መላኳን የዋይት ሐውስ የደኅንነት ጉዳዮች ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ማክሰኞ ዕለት ተናግረዋል።
"ድርድሩ ጠንካራና ጥልቅ ድርድር ነበር፤ ፍሬ ያፈራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል ጆን ኪርቢ።
የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማጂድ አል አንሳሪ ሰብዓዊ እርዳታን በተመለከተ ስምምነት ስለመደረሱ ቀደም ብለው አስታውቀው ነበር።
በዚህ ስምምነት መሠረት ሰብዓዊ እርዳታ ከዶሃ ዛሬ ረቡዕ ተነስቶ ግብጽ ይደርሳል። ከግብጽ ደግሞ ወደ ጋዛ እርዳታው በተመሳሳይ ቀን እንዲደርስ ይደረጋል። ይህ የሚሆነው ግን ለታጋቾች አስፈላጊ መድኃኒት ሲደርሳቸው ነው።
ከ132 በላይ የእስራኤል ታጋቾች በጋዛ በታጣቂዎች እጅ ናቸው።
ሐማስ መብረቃዊ ጥቃት በፈጸመበት ዕለት 1200 እስራኤላዊያንን ሲገድል፣ 240 የሚሆኑ ሰዎችን ደግሞ በእገታ ወስዶ ነበር።
የታጋች ቤተሰቦች ማኅበር እንደገለጸው ብዙዎቹ አሁን በሐማስ እጅ ያሉ ቤተሰቦቻቸው መድኃኒት ካልደረሳቸው ሕይወታቸው አደጋ ላይ ነው።
ባለፈው ሳምንት ቤኒያሚን ናታንያሁ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት ታጋቾቹ መድኃኒት በሚያገኙበት ሁኔታ ለመነጋገር የሞሳድ ኃላፊ ዴቪድ ባርኒ ኳታር መግባታቸውን ተናግረው ነበር።
የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ያለማቋረጥ በጋዛ ላይ በሰነዘረችው የአየር እና የምድር ጥቃት በትንሹ 24ሺህ ንጹሐን ተገድለዋል ይላል በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር። ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ሕጻናትና ሴቶች ናቸው።
የፍልሥጤም ባለሥልጣናት እንደሚሉት ደግሞ 85% የጋዛ ሕዝብ ከቀዬው ተፈናቅሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ኃላፊ በጋዛ ያለው ሁኔታ ‘ጊዜ የማይሰጥ’ ብለውታል።
ዓለም አቀፍ ጫናው በእስራኤል ላይ እየበረታ በመጣበት ሁኔታ ነው ይህ አዲስ ስምምነት በሐማስና በእስራኤል መካከል የተደረሰው።
በእስራኤል ጉዳይ ላይ የማትደራደረው አሜሪካ ሳይቀር እስራኤል እየሰነዘረች ያለችው ጥቃት ልኩን ያለፈ ነው፣ ናታንያሁ ጥቃታቸውን ጋብ ሊያደርጉ ይገባል ስትል ጫና ለማሳደር ሞክራ ነበር።
ሆኖም ቤኒያሚን ናታንያሁ ሐማስን ሳናጠፋ አንመለስም በሚል ግትር አቋም ይዘው ቆይተዋል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በጋዛ 90 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ በምግብ እጥረት ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታትን በመጥቀስ ተናግረው ነበር።
አክለውም ልጆች ተመጣጣኝ ምግብ በዚህ ጊዜ አለማግኘታቸው ሕይወታቸውን ሙሉ የሚከተላቸው ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ሲሉ አስገንዘበው ነበር።
“ተጨማሪ ምግብ፣ ተጨማሪ ውሃ፣ ተጨማሪ መድኃኒት እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች ወደ ጋዛ መግባት አለባቸው” ብለዋል ብሊንከን።
**
ማስታወሻ፡ በዚህ ዜና ላይ የሟቾች ቁጥር ማስተካከያ ተደርጎበታል።