በከፍተኛ ወንጀል የሚጠረጠሩ የቀድሞ የሱዳን ፖለቲከኞች ከእስር እያመለጡ እንደሆነ ተነገረ

ታትሟል

በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ጅምላ ግድያ የሚጠረጠሩ የቀድሞ የሱዳን ፖለቲከኞች ከእስር እያመለጡ እንደሆነ ተነገረ።

በኦማር አል በሽር አስተዳደር በተለያዩ ከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ያገለገሉት እና ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ተላልፈው እንደሚሰጡ ሲጠበቁ የነበሩት አሕመድ ሐሩን ከእስር ማምለጣቸው ተነግሯል።

ግለሰቡ ከእስር ቤት ማምለጣቸውን እራሳቸው በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ተናግረዋል።

እርሳቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከፍተኛ የቀድሞ ባለሥልጣናት አብረዋቸው ከማረሚያ ቤት እንዳመለጡ ተገልጿል።

በዚህ ሳምንት መጀመርያ በርካታ በሱዳን የሚገኙ እስር ቤቶች ተሰብረው እስረኞች ማምለጣቸው ሲነገር ነበር።

ከእነዚህ እስር ቤቶች መካከል ኦማር አል በሽር ታስረውበት የነበረው ኮበር ማረሚያ ቤት አንዱ ነው።

አሕመድ ሐሩንም ያመለጡት ከዚህ እስር ቤት መሆኑን ተናግረዋል።

የቀድሞው ከፍተኛ ባለሥልጣን አሕመድ ሐሩን በሱዳን ጣይባ ቲቪ በተላለፈ ሥርጭት እንዳረጋገጡት እርሳቸውና አብረዋቸው ታስረው የነበሩ ግለሰቦች እስር ቤቱን ለቀው ወጥተዋል።

“ለጊዜው አምልጠናል፤ የፍርድ ሒደቱ መቀጠል ሲችልና ስንፈለግ ለመምጣት ፍቃደኞች ነን” ብለዋል አሕመድ ሐሩን።

በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣናቸውን ያጡት ኦማር አል በሽር ለጊዜው የት እንደሚገኙ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የጦር ኃይሎች ሆስፒታል መግባታቸው ተዘግቦ ነበር።

እርሳቸውን ጨምሮ አምስት ከፍተኛ የቀድሞ የሱዳን ባለሥልጣናት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚፈለጉ ሲሆን ተላልፈው እንደሚሰጡም ተስፋ ተጥሎ ነበር።

ባለሥልጣናቱ በዘር ፍጅት፣ በጅምላ ግድያ፣ በጦር ወንጀል፣ በአስገድዶ መድፈርና ዳርፉር ላይ በተፈጸሙ አሰቃቂ ግድያዎች ተጠርጥረው እስር ላይ የነበሩ ናቸው።

ብዙዎቹ የዛጋዋ ማሳሊትና ፈር ሕዝቦችን ጨርሶ ከምድር ለማጥፋት ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል።

የ79 ዓመቱ ኦማር አል በሽር እስር ቤት ሰብረው ካመለጡ ባለሥልጣናት መሀል ይኑሩ ወይም ሆስፒታል ውስጥ ይገኙ ለጊዜው በይፋ የተባለ ነገር የለም።

አሕደም ሐሩን በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የቀረበባቸውን ክስ ያስተባበሉ ሲሆን ለእስር የተዳረጉት አል በሽርን ከሥልጣን የፈነቀለውን አብዮት ተከትሎ ነበር።

የአሁኖቹ ተዋጊ ጄኔራሎችን ጨምሮ የቀድሞ ከፍተኛ የሱዳን ባለሥልጣናት ከዳርፉር የጅምላ ግድያ ጋር በተያያዘ እጃቸው እንዳለበት ይነገራል።