ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ጦር ከሱዳን ጋር ተጋጭቷል መባሉ ሐሰት ነው አሉ
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጦር ከሱዳን ኃይሎች ጋር አልተጋጨም አሉ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ያሉት በሁለቱ አገራት አዋሳኝ ድንበር ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ በሱዳን ኃይሎች ላይ ጥቃት ከፍቷል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ትናንት ሐሙስ ሚያዚያ 13/2015 ዓ.ም. በአረብኛ ባወጡት መግለጫ ላይ ይህን አይነት ሐሰተኛ ሪፖርቶችን ያሚያሰራጩ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
“የኢትዮጵያ እና የሱዳን ሕዝቦች ብዙ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ በሚገኙበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ የሐሰት ውንጀላዎችን በማሰራጨት የፖለቲካ ጥቅም ለማሳካት የሚጥሩ ሰዎች አሉ” ብለዋል።
አንዳንድ ሪፖርቶች ኢትዮጵያ እና ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱበት ለም በሆነው አል-ፋሽቃ አካባቢ ማክሰኞ ዕለት የኢትዮጵያ ጦር በሱዳን ኃይሎች ላይ ጥቃት ከፍቷል ብለው ነበር።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በሱዳን ድንበር ሰፍሮ የሚገኘው ጦሯን ካነሳች በኋላ ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበትን የድንበር አካባቢዎችን ሠራዊቷን በማሰማራት የተቆጣጠረች ሲሆን፤ ባለሥልጣናቷም በቁጥጥራቸው ሥር ያስገቡት ሕጋዊ ግዛታቸው መሆኑን በመግለጽ ይዞታቸውን ሲያጠናክሩ ቆይተዋል።
ሁለቱ አገራት የሚወዛገቡበት አል-ፋሽቃ፣ ለም ሲሆነረ ከፍ ያለ የእርሻ ልማትና ተያያዥ ኢንቨስትመንቶች ይካሄዱበታል።
የሱዳንን እርምጃ ተከትሎ ኢትዮጵያ የድንበር አካባቢው ይዞታ ወደነበረበት እንዲመለስና ሁለቱ አገራት ችግሩን ቀደም ሲል ጀምረውት በነበረው የድንበር ኮሚሽን በኩል በውይይት እንዲፈቱት በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ነበር።
ባለፉት ቀናት በሱዳን የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎቹን መልሳ ለመያዝ ጦሯን አሰማርታለች የሚሉ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ከሱዳን ሲወጡ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዋናው መሥሪያ ቤት እና ካርቱም በሚገኘው ኤምባሲ አማካኝነት የኢትዮጵያውያንን ደኅንነት ለመጠበቅ እየሠራ ነው ብሏል።
በካርቱም ኤምባሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሁለት ቀናት በፊት በሱዳን እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት የኢትዮጵያውያን ሕይወት ስለማለፉ መረጃ ደርሶኛል ብሏል።
ኤምባሲው ግጭቱን ተከትሎ ምን ያህል ኢትዮጵያውያኖች ሕይወታቸው እንዳለፈ ያለው ነገር ባይኖርም ዜጎች የተቻላቸውን ሁሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።