ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኤቨረስት ላይ የሞተው ኬንያዊ ተራራ ወጭ አስከሬን በዚያው እንደሚያርፍ ቤተሰቦቹ ተናገሩ
ባለፈው ሳምንት የኤቨረስትን ተራራ ሲወጣ ህይወቱ ያለፈው ኬንያዊ አስከሬን በሞተበት ተራራ ላይ እንደሚያርፍ ቤተሰቦቹ ተናገሩ።
ጆሹዋ ቸሩዮት ኪሩይ ያለ ተጨማሪ ኦክስጅን ወደ ኤቨረስት ተራራ ጫፍ ለመድረስ ያለመ ተልዕኮን ለማሳካት እየሞከረ በነበረበት ወቅት ህይወቱ አልፏል።
የ44 አመቱ ተራራ ወጪ የኔፓል ዜግነት ካለው አስጎብኝው ጋር 8 ሺህ 849 ከፍታ ካለው የኤቨረስት ተራራ ለመድረስ 48 ሜትር ሲቀረው ነው በተራራው በረዷማ ክፍተት ወድቆ ህይወቱ ያለፈው።
ቤተሰቦቹ አስከሬኑን ከእንደዚህ አይነት ከፍታ ላይ አውጥቶ ለመውሰድ ለነፍስ አድን ቡድኑ በጣም አደገኛ ተግባር ነው ብለዋል።
ሆኖም የኔፓል የቱሪዝም ባለስልጣናት አስከሬኑን በተራራው ላይ መተው የአገሪቱን ህግ የሚጻረር ነው እያሉ ነው።
በአለማችን በከፍታው አንደኛ የሆነውን የኤቨረስት ተራራን መውጣት ልምድ ላላቸው ተራራ ወጭዎች ቢሆን እንኳን እጅግ አደገኛ እና ፈታኝ ነው።
ኪሩይ ከኔፓላዊው ናዋንግ ሼርፓ ጋር በመሆን የኤቨረስት ተራራን ያለ ተጨማሪ ኦክስጅን በመውጣት የመጀመሪያው አፍሪካዊ ለመሆን እየሞከረ ነበር።
የኪሩይ አስከሬን ቢገኝም ሼርፓ ያለበት እስካሁን አልታወቀም።
የተራራ ወጭው ቤተሰቦች ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ከመረመሩ፣ ሰፋ ያለ ምክክር እና ሁሉንም ነገሮች ከግምት ውስጥ ካስገቡ በኋላ አስከሬኑ በተራራው ላይ እንዲያርፍ የማድረግ “ከባድ ውሳኔ” ላይ መድረሳቸውን ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
“አስከሬኑን ከዚያ ከፍታ ላይ አውርዶ መውሰድ ለነፍስ አድን ቡድኑም ቢሆን አስጊ ነው። ቤተሰቡ የማንኛውንም ሰው ህይወት አደጋ ላይ መጣል አይፈልጉም” ይላል ከቤተሰቡ የወጣው መግለጫ
አክሎም “ኪሩይ ለተራሮች ጥልቅ ፍቅር ነበረው። በሚወደው ቦታ ላይ ማረፉን ማወቃችን መጽናናትን ይሰጠናል” ብሏል።
ቤተሰቡ በመዲናዋ ናይሮቢ እና በሪፍት ቫሊ ቀጠና በምትገኘው የትውልድ መንደሩ የሃዘን የመታሰቢያ ስርዓቶች እንደሚኖር ገልጸዋል።
አስከሬኑን ከተራራው ከማውጣት አደጋ በተጨማሪ ወደ አገር ቤት ወስዶ ለመቅበር ያስወጣል የተባለው ወጪም ጋር በተያያዘ ስጋቶች ሲነሱ ነበር።
አስከሬኑን ከተራራው አውጥቶ ወደ አገሩ ለማምጣት 190 ሺህ ዶላር ያስወጣል የተባለ ሲሆን ይህንንም ለማከናወን ስምንት ሰዎች እንደሚያስፈልጉ ተነግሯል።
ሆኖም የኔፓል ባለስልጣናት ኪሩይን አጅቦት የነበረው የጉዞ ወኪል በሚቀጥለው ተራራ በሚወጣበት ወቅት አስከሬኑ አውርደው እንደሚወስዱ ደብዳቤ ማስገባት እንዳለባቸው ውሳኔ አስተላልፈዋል።