ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ ራሳቸውን አስርበው ሲጸልዩ በነበሩ ሰዎች ሞት ከተጠረጠሩት አንዱ በእስር ላይ ሳለ ሕይወቱ አለፈ
በኬንያ ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ የአንድ እምነት ቡድን አባላትን በረሃብ ለሞት በመዳረግ ከተጠረጠሩ 30 ግለሰቦች መካከል አንዱ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እያለ ሕይወቱ አለፈ።
የእምነት ቡድን አባላቱ ለሞት የተዳረጉት 'የዓለም ፍፃሜ ተቃርቧል' በሚል 'እየሱስን እየጾሙ እንዲጠባበቁ' በእምነቱ መሪዎች ከተሰበኩ በኋላ ነበር።
በእነዚህ ሰዎች ሞት ከተጠረጠሩት መካከል አንዱ የሆነውና በእስር ላይ ሳለ ሕይወቱ ያለፈው ጆሴፍ ጁማ ቡኡካ፣ ከተወሰኑ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር በመሆን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እስራቸውን በመቃወም የረሃብ አድማ አድርጎ ነበር።
ከዚያም በደቡብ ምሥራቃዊቷ ከተማ ማሊንዲ ወደሚገኝ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን እዚያ እያለ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።
አቃቤ ሕግ፣ ሟቹ ከረሃብ አድማው ጋር በተያያዘ ውስብስብ የጤና ችግር ሳይሞት እንዳልቀረ ጥርጣሬ እንዳላቸው፤ ነገር ግን ትክክለኛውን የሞቱን መንስዔ ለማወቅ የአስክሬን ምርመራ ውጤት እየተጠባበቁ እንደሆነ በኬንያ የባህር ዳርቻዋ ከተማ ሞምባሳ ለሚገኘው ፍርድ ቤት አስረድተዋል።
ፖሊስ ክስተቱን በተመለከተ የሚያካሂደውን ምርመራ የቀጠለ ሲሆን የእምነቱ መሪ የሆኑትን ፖል ንቴንጌ ማኬንዜን ጨምሮ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ እስካሁን ክስ አልተመሰረተባቸውም።
ራስ ገዝ የሆነው ፓስተር እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ‘ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል’ ቤተክርስትያን አባላትን ራሳቸውን እስከ ሞት እንዲያስርቡ እንዳበረታቷቸው ይታመናል።
በዚህም ከሚያዚያ ወር አንስቶ ጫካ ውስጥ ከሚገኝ ጥልቅ ከሆኑ መቃብሮች 336 አስክሬኖች የወጡ ሲሆን ከ600 በላይ የሚሆኑ ሰዎች እስካሁን እንደጠፉ ናቸው።
ከዚሁ የእምነት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በአስክሬኖች ላይ በተደረገ ምርምራም የአንዳንዶች የውስጥ አካል መጥፋቱ ተነግሯል።
ሌሎች በረሃብ አድማ ላይ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎችም ሆስፒታል የገቡ ሲሆን በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ፍርድ ቤት በሚቀጥለው ማክሰኞ የእምነት ቡድኑ መሪ ማካንዜ ለተጨማሪ 60 ቀናት በእስር ይቆዩ አይቆዩ የሚለው ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
በኬንያዋ የባህር ዳርቻ ክሊፊ ውስጥ ሻካሆላ በተባለው ጫካ ውስጥ 'ጾማችሁ በሞት ኢየሱስን ታገኙታላችሁ' ተብለው የተሰበኩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አማኞች ሞት የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ከመጋቢት ወር ጀምሮ በዚሁ ስብከት ምክንያት በጾም ላይ ሆነው የሚገኙ በርካታ የእምነቱ ተከታዮችን ሕይወት ለማትረፍ በስፍራው ለወራት የቆየው የነፍስ አድን ሠራተኛ ያየሁት ነገር እንቅልፍ ነስቶኛል ብሏል።
የእምነቱ ተከታዮች እራሳቸውን በጾም በማድከም ከሞቱ መንግሥተ ሰማያት እንደሚገቡ በእምነቱ መሪ በመሰበካቸው፣ሕጻናትን ጨምሮ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች አስክሬን በፖሊስ ተፈልጎ መገኘቱ ይታወሳል።