ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፕሪሚየር ሊግ ግምቶች፡ ሊቨርፑል ቼልሲን ሲገጥም ዩናይትድ ከሜዳቸው ውጪ ዎልቭስን ይገጥማል
ትናንት ምሽት ቀጥሎ መካሄድ የጀመረው ሃያ ሁለተኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ቀጥሎ ይደረጋል።
ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች አርሰናል፣ ኒው ካስል፣ ፓላስ እና ሉተን ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሊቨርፑል እና ቼልሲን የሚያገናኘው ነው።
የቢቢሲው እግር ኳስ ተንታኝ ክሪ ሱቶን በውድድር ዓመቱ መጨረሻ የሊቨርፑል አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ቡድኑን እንደሚሰናበቱ ይፋ ማድረጋቸው በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ወይ? ሲል ይጠይቃል።
ማንቸስተር ሲቲ እያለ ነገሮች ለሊቨርፑል ቀላል አይሆኑም የሚለው ሱቶን፤ የክሎፕን ሽኝት ለማሳመር የሊቨርፑል ተጫዋቾች ዋንጫውን ለማንሳት የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ አስባለሁ ይላል።
ሱቶን የጨዋታ ግምቶቹን እንደሚከተለው አስቀምጧል።
ማንቸስተር ሲቲ ከ በርንሊ
አሠልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ ቡድኑን ይዞ ወደ ኢትሃድ ሲመለስ ከቀድሞ የክለቡ ደጋፊዎች ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግለት እጠብቃለሁ። ከዚህ ውጪ ግን ኮምፓኒ ምንም ይዞ አይመለስም።
ሲቲ ይህን ጨዋታ አሸንፎ ከመሪው ሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ይኖርበታል። የጋርዲዮላ ቡድን ይህን ጨዋታ በቀላሉ እንደሚያሸንፍም ይሰማኛል።
ግምት፡ ሲቲ 3 - 0 በርንሊ
ቶተነሃም ከ ብሬንትፎርድ
በዚህ የውድድር ዓመት ደካማ አቋም እያሳዩ ካሉ ቡድኖች መካከል አንዱ ብሬንትፎርድ ነው። የአይቫን ቶኒ መመለስ የአጥቂ መስመሩን እንደሚያጠናክር የሚያስማማ ቢሆንም፣ ብሬንትፎርድ ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ነጥብ የሚያገኝ አይመስለኝም።
ቶተነሃም እንዲሁ ሶን ሂዩንግ-ሚን ቢያጣም የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ለመዝለቅ፣ እንዲህ ዓይነት ጨዋታዎችን አሳማኝ በሆነ ሁኔታ ማሸነፍ ይጠበታል።
ግምት፡ ቶተነሃም 2 - 1 ብሬንትፎርድ
ሊቨርፑል ከ ቼልሲ
የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ይህ ነው።
ክሎፕ ከሊቨርፑል እንደሚሰናበቱ ይፋ ካደረጉ በኋላ የሚያደርጉት የመጀመሪያው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ነው።
ቼልሲዎች ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች አሸንፈዋል። ሰማያዊዎቹ ቀያዮቹን ሊፈትኑ እንደሚችሉ እገምታለሁ።
ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በሊጉ መሪዎች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።
የፖቸቲኖ ቡድን አንዳንዴ ሳይጠበቅ አስደናቂ ነገር ያሳያል፣ ይሁን እንጂ ይህን ጨዋታ ሊቨርፑል ሊያሸንፍ እንደሚችል እገምታለሁ።
ግምት፡ ሊቨርፑል 2 - 1 ቼልሲ
ዌሰት ሃም ከ ቦርንመዝ
የዚህን ጨዋታ ውጤት መገመት ትንሽ ይከብዳል። ዌስት ሃም በጉዳት ቡድኑ ሳስቷል። በሌላ በኩል ምንም እንኳ በሊቨርፑል በሰፊ የግብ ልዩነት ቢሸነፉም ቦርንመዝ ጥሩ አቋም ላይ የነበረ ቡድን ነው።
በመጀመሪያ ግጥሚያቸው 1 ለ 1 ነበር የተለያዩት። በዚህ ጨዋታም ነጥብ እንደሚጋሩ አስባለሁ።
ግምት፡ ዌሰት ሃም 1 - 1 ቦርንመዝ
ዎልቭስ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
አሁን አሁን ለአሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ እያዘንኩላቸው ነው። ቡድናቸው ቢያሸንፍ እንኳ በመጥፎ ጎኑ የሚነሳ ጉዳይ አያጣቸውም።
አጥቂያቸው ማርከስ ራሽፎርድ አሞኛል ብሎ ከልምምድ በመቅረት በምሽት መዝናኛ ቦታ ይታያል። አምበሉ ብሩኖ ደግሞ አንዳንድ ተጫዋቾች ጎል ፊት ሲደርሱ እየተስገበገቡ ኳስ አያቀብሉም ይላል።
ውጥረት ለማይለቻቸው ቴን ሃግ በሞለኒዩ የሚያደርጉት ግጥሚያ ቀላል አይሆንላቸውም።
ዩናይትድ በጉዳት ያጣቸውን እንደ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እና ካሴሚሮን መልሶ ቢያገኝም አሁንም በቡድኑ አልተማመንም። ጨዋታው በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።
ግምት፡ ዎልቭስ 1 - 1 ዩናይትድ