“መንግሥታችሁ አልቀበላቸውም ብሏል ተብለናል” በሳዑዲ አረቢያ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን

የፎቶው ባለመብት, HRW
በሳዑዲ አረቢያ የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለስ ቢፈልጉም እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ባለመቻላቸው አስከፊ በሆነ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እነዚህ ከ750 በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪነት እና ሌሎች ወንጀሎች ተከስሰው እስከ 15 ዓመት እስራት እንደተፈረደባቸውና የእስር ጊዜያቸውን እንደጨረሱ ከመካከላቸው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ያስረዳሉ።
ንጉስ [ለደህንነት ሲባል ስሙ ተቀይሯል] "ከ5 እስከ 15 ዓመት ተፈርዶብን ቅጣቱን ጨርሰናል። ወደ አገር ቤት ለለመለስ ተመዝግበን ነበር። ፎርሞችን ሞላን። ከዚያ በኋላ ግን እንዲወስዱን ስንጠይቃቸው፣ ‘መንግሥታችሁ አልቀበልም ብሏል’ አሉን” ሲል ስለሁኔታው ይናገራል።
ሌላኛው ስሙን መግለጽ ያልፈለገ በእስር ቤቱ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ በበኩሉ፣ “የእስር ጊዜያችንን ስለጨረሰን ከቆየንበት እስር ቤት አውጥተው ወደ ሌላ እስር ቤት ለዩን። ‘ከአሁን ወዲህ ነፃ ስለሆናችሁ ወደ አገራችሁ ትሄዳላችሁ’ ብለው ነው የለዩን። ሆኖም ግን እስከዛሬ ማንም ሊደርስልን አልቻለም” ሲል ቅሬታውን ገልጿል።
“የእስርቤቱ ዋና ኃላፊ መጥቶ አናግሮን ከበዓል በኋላ እንደምንሄድ ነገረን። ከዒድ በኋላ ጠብቀን ነበር ነገር ግን ምንም አዲስ ነገር የለም” የሚለው ዮሃንስ [ስሙ የተቀየረ] ከነበሩበት እስርቤት ወደ ሌላ የከፋ ቦታ ወስደው እንዳስቀመጧቸው ለቢቢሲ ገልጿል።
“ከነበርንበት እስር ቤት ወደ ሌላ ውሃ ወደሌለበትና የጦር መሳሪያ ማከማቻ ወደነበረ ቦታ ወስደውናል። መብራት እንኳን የለውም። ለምን ብለን ብንጠይቅ፣ ‘የእናንተ ጉዳይ እኛን የሚመለከት አይደለም። የእስር ግዜያችሁን ስለጨረሳችሁ የአገራችሁ መንግሥት ነው የሚመለከተው’ ብለውናል” በማለት ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Embassy Riyadh
"አስከፊ ሁኔታ ላይ ነን"
ኢትዮጵያውያኑ ከዚህ ቀደም ፍርዳቸውን ለመጨረስ ታስረው ከቆዩበት እስር ቤት ወደ ሌላ በጂዛን ልዩ ቦታ ኤዋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደሚገኝ እስር ቤት መወሰዳቸውን ይናገራሉ።
ከ750 በላይ ሰዎች መሰረታዊ አገልግሎት በማያገኙበት አንድ አዳራሽ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙም በመግለፅም ያሉበት ሁኔታ ለበሽታና ሞት ተጋላጭ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል።
“ሰዎች በየቀኑ ይሞቱብናል። ዛሬ ጠዋት ብቻ ሁለት ሰዎች ሞተዋል። ከትናንት ወዲያ ሌሎች ሁለት ሞተዋል። ይህንን የተቃወሙ 17 ሰዎችን ከዚህ አስወጥተው ውጭ ላይ አስረዋቸዋል” ይላል ዮሃንስ።
እነሱን ‘በሩን አንኳኩታቹሃል’ በሚል እንዲለዩ ያደረጉ ሲሆን፣ እንዲለዩ የተደረጉት በበኩላቸው “ሰው ሲሞትብን ታድያ ምን እናደርግ?” የሚል ምላሽ እንደሰጡ ያስረዳል።
የታጠቁት ጠባቂዎችም “በሩን ለመስበር ነው የሞከራችሁት” ብለው አስራ ሰባቱን ወደ ውጭ አውጥው እንዳሰሯቸው ዮሃንስ ጨምሮ ገልጿል።
ንጉስ በበኩሉ “የአእምሮአቸው ጤና የተቃወሰባቸው እና ራቁታቸውን የሚሄዱ ሰዎች አሉን። ቲቢ እና የስኳር በሽታ ያለባቸውም አሉ። ሕክምና የለም፤ ሌላ እርዳታም የለም። ጥፋታችን ምንድን ነው?” ሲል ይጠይቃል።
ስሙን መግለጽ ያልፈለገውና ከነ ዮሀንስ ጋር የሚገኘው ኢትዮጵያዊም አብረዋቸው ከነበሩ መካከል ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች እንዳሉ ተናግሯል።
"ለበሽታዎች ተጋልጠናል። በሆስፒታልም የምናገኘው ምንም እርዳታ የለም። ‘መንግሥታችሁ ነው የበደላችሁ እኛ ምንም አላጠፋንም’ ይሉናል” ሲልም አክሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ያውቅ ይሆን?
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ የቀድሞ ኢትዮጵያዊ ቆንስላ ሰራተኛ፣ የእስረኞቹ ጉዳይ እንደሚታወቅ እና ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን የጉዞ ሰነድ ለማዘጋጀት ጥረቶች እንደነበሩ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
እስረኞቹ በበኩላቸው የቅጣት ፍርዳቸውን ከጨረሱ አንድ ዓመት ቢያልፋቸውም በቆንስላው ሆነ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምንም አይነት ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ።
"አምባሳደሩ ብንደውልላቸው ስልካቸውን አያነሱም። ተወካዮቹ ወደዚህ መጥተው ሲያዩን ‘ይህን እናደርጋለን’ ብለው ቃል ይገቡልናል። ችግሩ የሳዑዲ መንግሥት እንደሆነም ይነግሩናል። የሳዑዲ መንግሥት በበኩሉ ችግሩ ያለው ‘በመንግሥታችሁ በኩል ነው’ ይለናል። በዚህ መካከል እኛ ተጎድተናል” ይላል ስሙን መግለጽ ያልፈለገው ኢትዮጵያዊ።
የሚመለከታቸው የቆንስላው አባለት ስለሁኔታቸው እንደሚያውቁ የሚገልፀው ንጉስ በበኩሉ ለቆንስላው ሰራተኞች ደጋግመው ቢደውሉም ምላሽ እንዳላገኙ ተናግሯል።
“ለተወሰነ ጊዜ መጥተው አይተውናል። ሆኖም ግን ‘ዛሬ እንመጣለን፤ ነገ እንመለሳለን’ ሲሉን ከቆዩ በኋላ ስልካቸውን እንኳን እያነሱልን አይደለም" ሲል አክሏል።
ወደ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ስልክ ቢደውሉም ምላሽ እንዳላገኙ የሚገልፀው ዮሀንስ በበኩሉ “ለሳዑዲ ባለስልጣናት ‘ምን እናድርግ?’ ብለን ስንጠይቃቸው 'አርፋችሁ ተቀመጡ፤ መንግሥታችሁ ከፈለገ መጥቶ ይወስዳቹሃል። ያለበለዚያ ቀይ መስቀል ይመጣል’ ይሉናል” ብሏል።
“በዚህ ቦታ ተቃውሞ ማድረግ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ የረሃብ አድማ ማድረግ ነው። ከዚህ በላይ አቅም የለንም” የሚሉት እነዚህ የእስር ጊዜያቸውን እንደጨረሱ የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ሲቪልና ወታደራዊ ባለስልጣናት ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
“የጥበቃ ካሜራ አላቸው። በረሃብ ተቃውሞ ለመግለፅ ስንሞክር መጥተው “ትፈታላችሁ” ይሉናል። ሞባይል ስልክ የለንም፤ መረጃ ማግኘትም አንችልም። በእስርቤቱ ውስጥ የግድግዳ ስልክ ስላለ ነው ወደ ቢቢሲ መደወል የቻልነው። የወደፊት ዕጣ ፈንታችን እንጃ. . . . .” ብሏል ዮሐንስ ሲቃ እየተናነቀው።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነን በሚሉት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ጅዳ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልኩ ሊነሳ አልቻለም።
ወደ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ደውለን ስለ ጉዳዩ ማብራርያ ብንጠይቅም፣ ጥያቄያችንን በኢሜል እንድንልክ ተነግሮናል።
ጥያቄያችንን ለሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ቢሮ በኢሜል ከ10 ቀን በፊት ኢሜል ብንልክም ምላሽ ወይ ማብራሪያ አልተሰጠንም።












