ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ሊቨርፑልን ለመግጠም ወደ ሜዳ የምንገባው “በእልህ ነው” አሉ
ባለፉት ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በተጨማሪ ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ጎሎች አምስት ነጥብ ያጣው ቡድን አሰልጣኝ፤ ሊቨርፑልን ለመግጠም ወደ ሜዳ የምገባው “በእልህ” ነው አሉ።
የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ተጫዋቾቻቸው በእልህ ተጫውተው ውጤት እንዲያመጡ አሳስበዋል።
በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ዩናይትድ ዛሬ አመሻሽ የዋንጫ ተፎካካሪ የሆነውን ሊቨርፑልን ይገጥማል።
ይህ “ታሪካዊ ጠላቶች” በሆኑ ክለቦች መካከል የሚደረገው ግጥሚያ በጉጉት ይጠበቃል።
ዩናይትድ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊነት ቦታን ለማግኘት፤ ሊቨርፑል ደግሞ ዋንጫውን ለማንሳት ትግል ላይ ይገኛሉ።
ዩናይትድ ባለፈው ሐሙስ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ በ99ኛ እና በ110ኛ ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ጎሎች በስታንፎርጅ ብሪጅ መሸነፉ ይታወሳል። ከዚያ በፊት ከብሬንትፎርድ በነበረው ጨዋታ 99ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠረበት ግብ ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት ተገዷል።
በእነዚህ ጨዋታዎች ያጧቸው 5 ውድ ነጥቦች የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፏቸውን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተባቸው ቴን ሃግ፤ ከሊቨርፑል ጨዋታ በፊት አስተያየት ሲሰጡ “ንቁ ሆነን የተሻለ ውሳኔ ወስነን ነጥብ ማግኘት አለብን” ብለዋል።
ቴን ሃግ በቼልሲ ሽንፈት ያደረሰባቸውን “ቁጭት ለሊቨርፑል ጨዋታ እንደሚጠቀሙበት” ጨምረው ተናግረዋል።
“በብስጭት ውስጥ ነው የምንሆነው። ከብስጭት ውስጥ ብዙ መነሳሳትን ማግኘት ይቻላል። የምናደርገውን እንደዛው ነው” ብለዋል አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ።
“በከፍተኛ ደረጃ መጫወት እንችላለን። ከፕሪሚየር ሊጉ የምርጦች ምርጥ ጋር መፎካከር እንችላለን። ይህን ማድረግ ከቻልን በመላው አውሮፓም ማድረግ እንችላለን” ብለዋል።
በአውሮፓ ከፍተኛ ሊግ ላይ ለመሳተፍ እስከ አምስተኛ ደረጃ መጨረስ ያለበት ዩናይትድ በአሁኑ ሰዓት አራተኛ ደረጃ ላይ ካለው አስተን ቪላ በ12 ነጥብ፤ አምስተኛ ደረጃ ላይ ካለው ቶተንሃም ደግሞ በ9 ነጥብ ርቆ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ትናንት ምሽት የሊጉ መሪነቱን በአርሰናል የተነጠቀው ሊቨርፑል ወደ ኦልድትራፎርድ ተጎዙ ዩናይትድን የሚያሸንፍ ከሆነ የሊጉ መሪነትን መልሶ ይረከባል።
የቢቢሲ የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ይህን ጨዋታ ሊቨርፑል 3 ለ 1 እንደሚያሸንፍ ግምቱን ሰጥቷል።