አሜሪካ ከጀማል ኻሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ ለሳዑዲው ልዑል ያለመከሰስ መብት ሰጠች

የፎቶው ባለመብት, AFP
አሜሪካ ከጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ ለቀረበው ክስ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ያለመከሰስ መብት አላቸው አለች።
የኻሾግጂ እጮኛ በጋዜጠኛው ግድያ ልዑል አልጋ ወራሹን ጨምሮ በሌሎች ላይ ክስ መስርታ ነበር። አሜሪካ ግን ልዑል አልጋ ወራሹ ያለመከሰስ መብት አላቸው ብላለች።
የሳዑዲ አስተዳደርን በጥብቅ በመተቸት ይታወቅ የነበረው ኻሾግጂ፣ እአአ 2018 ላይ ቱርክ ኢስታንቡል በሚገኝ የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ መገደሉ ይታወሳል።
የአሜሪካ የደኅንነት ተቋም የጋዜጠኛውን ግድያ ያዘዙት ልዑል አልጋ ወራሹ መሆናቸውን ያምናል።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሞሐመድ ቢን ሰልማን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አዲስ ኃላፊነት በመውሰዳቸው በወንጀሉ አይጠየቁም ብሏል።
ልዑል አልጋ ወራሹ በጋዜጠኛው ሞት እንደማይጠየቁ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የኻሾግጂ እጮኛ ሃቲስ ሴንጊዝ በትዊተር ገጿ ላይ “ጀማል በድጋሚ ዛሬም ሞቷል” ስትል ጽፋለች።
ሃቲስ ሴንጊዝ እና የመብት ተሟጋች ቡድን ሞሐመድ ቢን ሰልማን እና የሳዑዲ ባለሥልጣናት የአሜሪካ ነዋሪ እና የሳዑዲ ዜጋ የነበረውን ኻሾግጂን አፍኖ በመያዝ፣ በመመረዝ፣ በማሰቃየት እና በመግደል ክስ መስርተዋል።
ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን እአአ 2017 በአባታቸው ንጉሥ ሰልማን ቢን አብዱላዚዝ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ተብለው የተሾመው የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ የ37 ዓመቱ ፖለቲከኛ ይፋዊ ባልሆነ ሥልጣን ሳዑዲን እያስተዳደሩ ይገኛሉ። ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣንን ይዘዋል።
ሞሐመድ ቢን ሰልማን በጋዜጠኛው ግድያ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደሌላቸው ይገልጻሉ።
የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት “የወቅቱ በሥልጣን ላይ ያለ የውጭ አገር ባለሥልጣን” ልዑል አልጋ ወራሹ “በያዙት ሥልጣን ምክንያት ከሚቀርቡባቸው ክሶች በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ያለመከሰስ መብት ይኖራቸዋል” ማለቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የባይደን አስተዳደር ልዑል አልጋ ወራሹ በወንጀሉ አይጠየቁም ይበል እንጂ ከወንጀሉ ነጻ ናቸው የሚል ውሳኔ እንዳልሰጠ መሰመር አለበት ሲል የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
ለሞሐመድ ቢን ሰልማን የተሰጠው ያለመከሰስ መብት የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆችን በመከተል በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተላለፈ ውሳኔ መሆኑን የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ በመግለጫቸው ገልጸዋል።
የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋዜጠኛው የተገደለው የአገሪቱ ባለሥልጣናት እውቅና ሳይኖራቸው እና ፍቃድ ሳያገኙ ኻሾግጂን ወደ ሪያድ ለመመስ ጫና ለመፍጠር ሙከራ ባደረጉ የደኅንነት አባላት የተፈጸመ ነው ብሎ ነበር።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ግን የአሜሪካ የደኅንነት ተቋም ሲአይኤ በጋዜጠኛው ግድያ ልዑል አልጋ ወራሹ “ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ በእርግጠኝነት” ተባባሪ እንደነበሩ ደምድሟል ብለዋል።
የጋዜጠኛው ግድያ እአአ 2018 ላይ ዓለምን ብዙ ካነጋገሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ግድያው የልዑል አልጋ ወራሹን ስም ያጠለሸ ነበር።
በወቅቱ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ የነበሩት ጆ ባይደን ሥልጣን ሲይዙ ሳዑዲን ‘የተገለለች’ አገር እንደሚያደርጓት ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በጊዜ ሂደት ከሳዑዲ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ዳግም በማጤን ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሪያድ ተጉዘው ነበር።
ባይደን ሳዑዲ በደረሱ ወቅት ከአልጋ ወራሹ ጋር እጅ ለእጅ ተገጫጭተው ሰላምታ መለዋወጣቸው ከጋዜጠኛው ግድያ በኋላ ለሳዑዲ መንግሥት እውቅና መስጠት ነው ተብለው ተነፍቀው ነበር።












