አየርላንድ የጋዛን ጭፍጨፋ ለፍርድ እንዲቀርብ በመደገፏ ምክንያት እስራኤል ኤምባሲዋን ልትዘጋ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አየርላንድ ፍልስጤምን በነጻ አገርነት እውቅና በመስጠት እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት በእስራኤል ያቀረበችው የጋዛን ጭፍጨፋ ክስ በመደገፏ ምክንያት እስራኤል በደብሊን የሚገኘውን ኤምባሲ ልትዘጋ ነው።

"የአየርላንድ መንግሥት ጽንፈኛ ጸረ- እስራኤል ፖሊሲዎች" እያካሄደ ነው ሲል የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተችቷል።

ሚኒስትሩ ጌዲዮዎን ሳር የአየርላንድ ሪፐብሊክ "እያንዳንዷን ቀይመስመር" አልፏል ብለዋል።

አየርላንድ ቀደም ሲል ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት መወሰኗን ተከትሎ በደብሊን ተቀማጭነታቸውን ያደረጉት የእስራኤል አምባሳደር ለምክክር ተጠርተው እንደነበር ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።

የአሁኑ ውሳኔ የተላለፈው ደቡብ አፍሪካ በአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው ለሚለው ክስ አየርላንድ ድጋፍ መስጠቷን ተከትሎ ነው።

"አየርላንድ በእስራኤል ላይ እየወሰደቻቸው ያሉ ድርጊቶች እና ጸረ-ሴማዊ ትርክቶች የአይሁድን መንግሥት ዕውቅና የነፈገ እና ዕኩይ ምስል የሰጠ ነው" ብለዋል ሚኒስትሩ።

"እስራኤል ሃብቷን ኢንቨስት ስታደርግ በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነቷን ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም መንግሥታቱ ለእስራኤል ያላቸውን አመለካከት እና ድርጊት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው" ብለዋል።

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሞን ሃሪስ በምላሹ እስራኤል በአየርላንድ የሚገኘውን ኤምሳቢዋን ለመዝጋት መወሰኗ "በጣም የሚያሳዝን ነው" ብለዋል።

አየርላንድ ጸረ-እስራኤል ናት የተባለውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውድቅ አድርገውታል።

የአየርላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሚሼል ማርቲን አየርላንድ በእስራኤል የሚገኘውን ኤምሳቢዋን የመዝጋት እቅድ የላትም ብለዋል።

ሚሼል በደብሊን የሚገኘውን ኤምባሲውን ለመዝጋት የእስራኤል መንግሥት መወሰኑን እንዳሳወቃቸው ገልጸዋል።

"የዲፕሎማሲያዊ መስመሮችን እና ግንኙነችን በመጠበቅ አስፈላጊነት አምናለሁ እናም ይህ ውሳኔ መወሰዱ ያሳዝናል" ብለዋል።

"በመካከለኛው ምስራቅ ግጭት ላይ የአየርላንድ አቋም በአለም አቀፍ ህግ መርሆዎች እንዲሁም ሁሉም መንግሥታት የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግ ያክብሩ በሚለው ግዴታ የተመሰረተ ነው" ብለዋል።

በጋዛ ያለው ጦርነት መቀጠሉ እንዲሁም "የንጹሃን ህይወት መቀጠፉ ተቀባይነት የሌለው እና የዓለም አቀፍ ህግን የሚጻረር ነው" ብለዋል።

አክለውም "ይህ በጋዛ የፍልስጤም ህዝብ በጋራ ቅጣት እየተፈጸመበት እንደሆነ አሳይ ነው። በአፋጣኝ የተኩስ አቁም መደረግ አለበት። ታጋቾች መፈታት እና በጋዛ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ያስፈልጋል" ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።

አየርላንድ እና እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በዚህ ውስጥ መሰረታዊ ነጥቡ ባለመስማማት ተስማምተን እንቀጥላለን" ብለዋል።