ትራምፕ ሊታሰሩ ይችሉበታል በተባለው ቀን የአሜሪካ ፖሊስ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል

የፖሊስ አባል ሞትርስይክል ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እየተደረገባቸው ካለው ምርመራ ጋር ተያይዞ በዚህ ሳምንት የሚታሰሩ ከሆነ ሊፈጠር የሚችለውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር በተለያዩ ከተሞች የአሜሪካ ፖሊስ ዝግጅቱን እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል።

ባለስልጣናት በኒውዮርክ፣ ዋሽንግተን ዲሲና ሎሰአንጀሎስ ከተሞች የተሰማራው የፖሊስ ሃይልን አጠናክረዋል።

የማንሃታን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትራምፕ ከአንዲት የወሲብ ፊልም ተዋናይት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለመደበቅ ገንዘብ ከፍለዋታል የሚል ክስ ሊመሰርት ይችላል።

ይህ የሚሆን ከሆነ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለነበረ ሰው በዚህ አይነቱ የወንጀል ጉዳይ ሲከሰስ የመጀመሪያው ይሆናል።

የትራምፕ ጉዳይ ሊታይ ይችላል በተባለበት የማንሃታን ፍርድ ቤት አከባቢ ትላንት ሰኞ የብረት ማገጃዎች ተተክለዋል። የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በስፋት ግምታቸውን እንዳስቀመጡት ከሆነ በፍርድ ቤቱ ትራምፕ ክስ ሊመሰረትባቸው፣ የጣት አሻራ ሊሰጡበትና ፎቶግራፍ ሊነሱበት ይችላሉ።

በከተማው በሚገኘው ትራምፕ ታወር አቅራቢያም የተሰማራው የፖሊስ ቁጥር ከወትሮው ጨምሮ ታይቷል።

የሲቪል ልብስ የሚለብሱ መርማሪዎችን ጨምሮ ሁሉም የኒውዮርክ ፖሊስ ክፍል አባላት ዛሬ ማክሰኞ የደንብ ልብሳቸውን እንዲለብሱ እና ለግዳጅ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።የኒውዮርክ ፖሊስና ኤፍቢአይ የጋራ ጸረ ሽብር ሃይል ከየቀድሞና የወቅቱን ፕሬዚዳንት የመጠበቅ ተልዕኮ ካለው የአሜሪካ ሚስጥራዊ አግልግሎት ጋር ትራምፕ ሊታሰሩ ሰለሚችሉበት ሁኔታ መምከራቸው ተሰምቷል።

በዋሽንግተን የሚገኘው እና ህግ አውጪዎችን የሚጠብቀው የካፒቶል ፖሊስ የአስቸኳይ ጊዜ እወጃ ዛሬ ማክሰኞ ሊያውጅ እንሚችል ምንጮች ለአሜሪካው ሲቢኤስ ተናግረዋል።

የተሰጠው ትዕዛዝ ከሌሎች የህግ አስከባሪዎች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው።

ሌሎችም የጸጥታ ሃይሎች በተጠንቀቅ ሊቆሙ እንደሚችሉም ተነግሯል።

በሎስአንጀለስ የግዛቱና የፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች የትራምፕ ደጋፊዎች የሚያደርጉትን ተቃውሞ ለመከላከል መዘጋጀታቸው ተዘግቧል።

ባለፈው ቅዳሜ ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ማክሰኞ ልታሰር እችላለሁ ብለው መጻፋቸውን ተከትሎ የአሜሪካ የህግና አስተዳደር ባለስልጠናት እየተሰነዘረ ያለውን ዛቻ የአሜሪካ የደህንነት ተቋም እየመረመረ ይገኛል።

አብዛኛው ዛቻ ያነጣጠረው ትራምፕ ላይ ክስ እንደሚመሰርቱ በሚጠበቁት የማንሃታን አውራጃ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አሊቪን ባራግ ላይ ነው።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ለሰራተኞቻቸው በኢሜይል በላኩት መልዕክት ትራምፕ በተመሳሳይ ቀን ደጋፊዎቻቸው መቃውም እንዳለባቸው መጻፋቸውን ገልጸዋል።

“በመኮንኖቻችን ላይ ዛቻ ወይም ወከባ የማድረስ ሙከራን አንታገስም” ሲሉም ጽፈዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ትራምፕ ላይ ክስ ለመመስረት በቂ ማስረጃ መኖሩን የሚመረምር የዳኞች ቡድን አቋቁመዋል።

ጉዳዩም ትራምፕ ስቶርሚይ ዳኒልስ ከተባለች የወሲብ ፊልም ተዋናይት ጋር ያላቸውን ግኙነት ለመደበቅ 130 ሺህ ዶላር ከፍለዋል መባሉ ላይ የሚያጠንጥን ነው።

ይህም የሆነው ትራምፕ እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ምርጫ ለመሳተፍ ሲዘጋጁ ተዋናይቷን ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ዝም ለማሰኘት ነው። ሆኖም ፕሬዝዳንቱ ከተዋናይቷ ጋር ግንኙነት የለኝም ይላሉ።