በአሜሪካ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ሜክሲኳዊ ዕጽ አዘዋዋሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

ራፋኤል ካሮ ኬንቴሮ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

አሜሪካ በጥብቅ ስትፈልገው የነበረው ሜክሲኳዊ ዕጽ አዘዋዋሪ ራፋኤል ካሮ ኬንቴሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የሜክሲኮ ባሕር ኃይል አስታወቀ።

ኬንቴሮ እአአ በ1985 አሜሪካዊውን የዕጽ ዝውውር ተቆጣጣሪ ተቋም ባልደረባን በማፈን፣ በማሰቃየት እና በመግደል ይከሰሳል። 

የሜክሲኮ ባሕር ኃይል ይህን ዋነኛ ዕጽ አዘዋዋሪ ልዩ ሥልጠና በወሰደ አነፍናፊ ውሻ ታግዞ በአገሪቱ ሲናሎዋ በተባለው ግዛት ውስጥ ባደረገው አሰሳ መያዙን ገልጿል።

አሜሪካ የ69 ዓመቱ የዕጽ አዘዋዋሪዎች መሪ ተላልፎ እንዲሰጣት በአስቸኳይ እንደምትጠይቅ ተገልጿል።

“የትኛውም ሰው አሜሪካዊ የሕግ አስከባሪን አፍኖ፣ አሰቃይቶ እና ገድሎ መደበቂያ ማግኘት አይችልም። የሜክሲኮ ባለሥልጣናት ራፋኤል ካሮ ኬንቴሮን በመያዛቸው ጥልቅ ምስጋና እናቀርባለን” ብለዋል የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ።

ኬንቴሮ ትልቅ ስም ያለውን ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን ጓድላሃራን ከመሰረቱ ሦስት ግለሰቦች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የዕጽ ዝውውሮችን የሚከላከለ ተቋም አባልን ከገደለ በኋላ 28 ዓመታት እስር ተፈርዶበት ነበር።

በወቅቱ የዚህ የሕግ አስከባሪ መገደል በአሜሪካ እና በሜክሲኮ መካከል ቁርሾ ፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ‘ናርኮስ፡ ሜክሲኮ’ በሚል ርዕስ በድራማ መልክ ኔትፍሊክስ ላይ ቀርቧል።

እአአ 2013 ላይ የሜክሲኮ ፍርድ ቤት በግድያው ወንጀለኛ ተብሎ የ40 ዓመት እስር ተፍርዶበት የነበረውን ኬንቴሮን፤ የተላለፈበትን የእስር ቅጣት አንስቶለት ነበር።

ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ የተደረገ ቢሆንም ኬንቴሮ ከእስር ቤት ወጥቶ ስለነበረ መልሶ በቁጥጥር ሥር ማዋል ሳይቻል ቀርቷል።

አሜሪካ ኬንቴሮ ከእስር እንደተለቀቅ በፍጥነት ወደ ዕጽ ማዘዋወር ሥራው መመለሱን ገልጻ፤ ኬንቴሮን መያዝ የሚያስችል መረጃ ለሚሰጥ 20 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ ብላ ነበር።

የኬንቴሮ መያዝ ባለፈው አስርት ዓመታት ውስጥ የዕጽ ዝውውር ተቆጣጣሪው አካል ስኬቶች መካከል አንዱ ነው ሲሉ የቀድሞ የአሜሪካው የፀረ ዕጽ ዝውውር ተከላካይ አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊ ማይ ቪጂል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።