በዓለም ዋንጫ ሴቶች በዳኝነት የመሩት የመጀመሪያው ጨዋታ ተደረገ

ሮናልዶ፣ ፍራፓርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስቴፋኒ ፍራፓርት በዛሬው ጨዋታ የዓለም ዋንጫን ጨዋታን በመዳኘት የመጀመሪያዋ ሴት ዳኛ ትሆናለች
ታትሟል

በኳታር እየተካሄደ ባለው የዓለም ዋንጫ ውድድር ሐሙስ ኅዳር 22/2015 ዓ.ም. ምሽት ኮስታ ሪካ እና ጀርመን ያደረጉት የምድብ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በሴት ዳኞች ተመርቷል።

በጨዋታው ለዋንጫው ከሚጠበቁት ቡድኖች መካከል አንዷ የነበረችው ጀርመን ኮስታ ሪካን 4 ለ 2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ብትችልም ከውድድሩ ተሰናብታለች።

ጨዋታውን በብቃት በመምራት ስቴፋኒ ፍራፓርት በወንዶች የዓለም ዋንጫ ላይ በመዳኘት የመጀመሪያዋ ሴት ሆናለች።

ፈረንሳዊቷ ዳኛ ባለፈው ማክሰኞ ሜክሲኮ እና ፖላንድ ባደረጉት ጨዋታ አራተኛ ዳኛ በመሆን በውድድሩ የመጀመሪያዋ ሴት ዳኛ ሆናለች።

ፍራፓርት ከውድድሩ በፊት ለቢቢሲ ስፖርት ጨዋታውን በተመለከተ “ጫናውን እናውቀዋለን” ስትል ተናግራለች።

“ራሳችንን ግን የማንለውጥ ይመስለኛል። መረጋጋት፣ ትኩረት መስጠት እና ስለ ሚዲያ እና ስለ ሌላው ነገር ብዙ ባለማሰብ በሜዳ ላይ ብቻ አናተኩራለን” ብላለች።

ሐሙስ ኅዳር 22/2015 ዓ.ም. በአል ባይት ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ፍራፓርትን በማገዝ ረዳት ዳኞች የሆኑት ብራዚላዊቷ ኑዛ ባክ እና ሜክሲኳዊቷ ካረን ዲያዝ ናቸው።

በሴትነቷ ምክንያት ከተጫዋቾች፣ ከአሰልጣኞች ወይም ከደጋፊዎች አስተያየት ተሰጥተወት እንደሆነ የተጠየቀችው ፍራፓርት፣ “[ዳኝነት] ከጀመርኩ ጊዜ ጀምሮ ከቡድኖች፣ ከክለቦች እና ከተጫዋቾች ድጋፍ እያገኘሁ ነው።  ሁልጊዜም ስታዲየም ውስጥ አቀባበል ስለሚደረግልኝ ራሴን እንደማንኛው ዳኛ እመለከታለሁ። አሁንም ተመሳሳዩ እንደሚጠብቀኝ አስባለሁ” ስትል መልሳለች።

ስቴፋኒ ፍራፓርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስቴፋኒ ፍራፓርት

ፍራፓርት እአአ በ2020 የወንዶች ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታን በመዳኘት የመጀመሪያዋ ሴት ሆናለች።

የ38 ዓመቷ ዳኛ እአአ በ2019 የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ሊቨርፑል እና ቼልሲ ሲጫወቱ በመዳኘት ታላቅ የወንዶች የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ውድድርን ለመምራት የቻለች የመጀመሪያዋ ሴት ለመሆንም በቅታለች።

ሦስት ሴቶች (ፍራፓርት፣ ርዋንዳዊቷ ሳሊማ ሙካንሳንጋ እና ጃፓናዊቷ ዮሺሚ ያማሺታ) የኳታሩን የዓለም ዋንጫን እንዲመሩ ከተመረጡት 36 ዳኞች መካከል ይገኙበታል።

ከተጀመረ ሁለት ሳምንት ሊሆነው የተቃረበው በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የዓለም ዋንጫ የምድብ ውድድሮች ነገ አርብ ተጠናቀው፣ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ይጀመራሉ።

በአረቡ ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ የዓለም ዋንጫ፣ ጨዋታ በሴት ዳኞች ከመመራቱ በተጨማሪ በርካታ ልዩ ክስተቶች እየታየበት ነው።

የዓለም ዋንጫው በበረሃማዋ ኳታር የሚካሄድ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ውድድሩ ይካሄድበት ከነበረው ወቅት በተለየ ጊዜ እየተከናወነ ይገኛል።

አስካሁን ባለው የውድድሩ መስተንግዶ በቢሊዮን ዶላሮችን አውጥታ የተዘጋጀችው ኳታር ስኬታማ እየሆነች እንደሆነ ይነገራል።