ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ያለውን የሠራዊት ቁጥር መቀነሱን አሳወቀ
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ያለውን የሠራዊት ቁጥር እየቀነሰ በአካባቢው አንድ ብርጌድ ብቻ እንደሚያስቀር ይፋ አደረገ።
"ጉልህ ቁጥር ያለው ኃይል" በጋዛ እንደሚቆይም ጦሩ አክሏል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ፒተር ለርነር “ይህ በጦርነቱ ውስጥ ሌላ እርምጃ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ውሳኔው ጦርነቱ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ መሆኑን ከመጠቆም ይልቅ እርምጃው ታክቲካዊ ነው ተብሏል።
በተመሳሳይ እሑድ ዕለት እስራኤል እና ሐማስ አዲስ የተኩስ አቁም ድርድር ለማስጀመር ልዑካቸውን ወደ ካይሮ ልከዋል።
ሐማስ መስከረም 26 ደንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ 1ሺህ 200 ሰዎችን ከገደለ እና ከ250 በላይ ሰዎችን አግቶ ከወሰደ ስድስት ወራት ተቆጥረዋል።
እስራኤል በጋዛ 130 ታጋቾች እንዳሉ ስትናገር ቢያንስ 34ቱ ሳይሞቱ እንዳልቀረ ይገመታል።
ከዚያን ወዲህ እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ጥቃት ከ33 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሲቪሎች ናቸው።
'ጦርነቱ አላበቃም'
ሌተር ኮሎኔል ለርነር እንደተናገሩት ወታደሮቹ የሚቀነሱበት ምክንያት ወታደሮቹ በኻን ዮኒስ ተልዕኳቸውን ስላጠናቀቁ ነው።
ኻን ዮኒስ ለወራት በእስራኤል የቦምብ ጥቃት ሲደርስባት የቆየች ሲሆን ከተማዋ እና አካባቢዋ በእጅጉ ወድመዋል።
ሌተር ኮሎኔል ለርነር "ጦርነቱ አላበቃም። ጦርነት ሊያበቃ የሚችለው ታጋቾቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ እና ሐማስ ሲጠፋ ብቻ ነው" ብለዋል።
"የኃይሉ ቅነሳ ቢኖርም ግን መከናወን ያለባቸው ተጨማሪ ሥራዎች አሉ። ራፋህ ጠንካራ ይዞታቸው እንደሆነች ግልጽ ነው። የሐማስን አቅም በያለበት ማፍረስ አለብን።"
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ በበኩላቸው ይህ “እረፍት እና ማሻሻያ” ነው ካሉ በኋላ “ለወታደሮቹ አዲስ ዘመቻ መምጣትን የሚያመለክት አይደለም” ብለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ግን ወታደሮቹ እየወጡ ያሉት “ለተከታይ ተልዕኮቻቸው ለመዘጋጀት ነው” ብለዋል።
በዃን ዮኒስ ያስመዘገቡት ውጤት እጅግ አስደናቂ ነው ብለዋል። ሐማስ በመላው ጋዛ ወታደራዊ ድርጅት ሆኖ መንቀሳቀሱን አቁሟል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የተኩስ አቁም ግፊት እየጨመረ ሲሆን የእስራኤል የቅርብ አጋር የሆነችው አሜሪካ ለጋዛ ጦርነት ቀጣይነት ያለው ድጋፏ መሠረት የሚያደርገው እርዳታን ለመጨመር እና የሲቪል ሞትን ለመከላከል "በተወሰኑ ተጨባጭ እርምጃዎች" ላይ የተመሠረተ መሆኑን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አሳውቃለች።
ስድስት ወራት ያስቆጠረውን ጦርነት አስመልክቶ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንደተናገሩት አገራቸው “ለድል አንድ እርምጃ ቀርቷታል” ብለዋል። የእስራኤል ታጋቾች ካልተለቀቁ የተኩስ አቁም እንደማይኖርም አስረድተዋል።
"የጦርነቱ ስኬቶች ትልልቅ ናቸው። ከፍተኛ አዛዦችን ጨምሮ ከ24 የሐማስ ሻለቃ ጦር 19ኙን አስወግደናል" ብለዋል።
በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ቅዳሜ ዕለት ኔታንያሁን በመቃወም አደባባይ የወጡ ሲሆን በጋዛ ታግተው ያሉትን ለማስለቀቅ ስምምነት እንዲደረስም ጠይቀዋል።
የመንግሥት ተቃዋሚዎች የታጋቾች ቤተሰቦችን ተቀላቅለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የታጋቹ ኤላድ ካትዚር አስከሬን ካገኘ ከሰዓታት በኋላ ነው በቴል አቪቭ እና በሌሎች ከተሞች ሰልፎቹ የተካሄዱት ።
በቴል አቪቭ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ 100 ሺህ ሰዎች መገኘታቸውን አስተባባሪዎች ቢገልጹም ሌሎች ደግሞ ቁጥሩን ወደ 45 ሺህ ገምተዋል።
እሁድ አመሻሽ ላይ ተጨማሪ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኢየሩሳሌም ለተቃውሞ ወጥተዋል።