ጀርመን፡ በ10 ደቂቃ ልዩ የስርቆት ጥበብ የተዘረፉት የአልማዝና ዕንቁ ጌጣጌጦች ተገኙ

በወቅቱ ከተዘረፉት አንዱ ይህ በአልማዝ የተንቆጠቆጠ ጌጥ ይገኝበታል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በወቅቱ ከተዘረፉት አንዱ ይህ በአልማዝ የተንቆጠቆጠ ጌጥ ይገኝበታል
ታትሟል

በዘመናዊ ጀርመን የዘረፋ ታሪክ ይህ በዓይነቱ የመጀመርያው ነው የተባለ ዘረፋ ላለፉት ሦስት ዓመታት የጀርመን ዋንኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ነበር። 

ዘራፊዎቹ አንድ ሙሉ ሙዝየም ገብተው እጅግ ውድ ጌጣጌጦችን ሙልጭ አድርጎ ለመዝረፍ የወሰደባቸው ጊዜ በድምሩ ከ10 ደቂቃ ያነሰ ነበር። 

ይህ የሆነው ደግሞ በምሥራቅ ጀርመን ጥብቅ ጥበቃ ይደረግለታል በሚባለው ድሬስደን ግሪን ቮልት ሙዝየም ነበር። 

ድርጊቱ የተፈጸመው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2019 ዓ/ም ነው። 

በወቅቱ የዚህ የተቀናጀ ዘረፋ ስኬታማነት ዓለምን ያነጋገረ ነበር። አንዳንዶች ይህ በፊልም እንጂ በዕውን የሚሆን ነገር እንዳይደለ ሲናገሩም ነበር። 

ዘራፊዎቹ ስኬታማ የዘረፋ ተግባር ለመፈጸም የተጠቀሙት ዘዴ በሌላኛው የሙዝየሙ ክፍል መጠነኛ የእሳት አደጋ በማስነሳት ነው። 

ከዚያ በኋላ አብዛኛዎቹን የክትትል ካሜራዎች ከጥቅም ውጭ በማድረግ በልዩ መዶሻ የጌጣጌጥ ማስቀመጫ መስታወቶችን ሰብረዋል። 

ከዚያም ከከበሩ ማዕድኖች፣ በዕንቁና አልማዞች የተንቆጠቆጡ ቅርሶችን በልዩ ጥንቃቄ  ወስደዋቸዋል። 

የልዩ ጌጣጌጦቹ ዋጋ በትንሹ 130 ሚሊዮን ዩሮ ይጠጋል። 

ከዋጋቸውም በላይ በጀርመን ታሪክ የሚሰጣቸው ቦታ ልዩ በመሆኑ በአገሬው ዘንድ ዘረፋው ትልቅ ዜና ሆኖ ቆይቷል። 

ዘራፊዎቹ በ10 ደቂቃ ዝርፍያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በአውዲ ሞዴል መኪና ገብተው ተሰውረዋል። 

የተጓዙበትን አውዲ መኪና በአንድ የመኪና መቆምያ ማዕከል እሳት ለቀውበት ተሰውረዋል።

በአልማዝ ያጌጠ የንሥር ቅርጽ ያለው ቅርስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከተዘረፉት መሀል ይህ ውድ ጌጥ ይገኝበታል።

እነዚህ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ናቸው የተባሉት በዕንቁና አልማዝ የተንቆጠቆጡት ጌጣጌጦች በርካታ ሲሆኑ አሁን ፖሊስ በእጄ አስገብቻቸዋለሁ ያለው 31ዱን ብቻ ነው። 

እጅግ ውድ ናቸው የተባሉት ጌጣጌጦችን ፖሊስ ማግኘት የቻለው በፍርድ ሂደት ላይ ከሚገኙት የተጠርጣሪ ጠበቆች ጋር ሰፊ ምክክርና ድርድር ካደረገ በኋላ ነው የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል። 

ይህን ዘረፋ ፈጽመዋል የተባሉት ስድስት ወጣት ወንዶች በአሁኑ ጊዜ ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን እያየው ነው። 

እነዚህ ጌጣጌጦችን በ1723 ዓመተ ምሕረት የሰበሰባቸው የሳክሰን ገዥ የነበረው ንጉሥ አውጉስተስ ነበር።

ከዚያ በኋላ ለዓመታት በጀመርን ቤተ መንግሥት ተቀምጠው ነበር። 

የጀርመን ባለሥልጣናት በዘረፋው ማግስት እንዳመኑት ይህ ዘረፋ የተቀነባበረው እጅግ በረቀቀ መንገድ ፍጹም ጠንቃቃ በሆኑ ስልጡን ዘራፊዎች ነው። 

ግሪን ቮልት መካነ ቅርስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዘረፋው የተፈጸመበት ግሪን ቮልት ሙዝየም

አሁንም ገና ያልተመለሱ በርካታ ጌጣጌጦች የቀሩ ሲሆን ከነዚህ መሀል ‘ድሬስደን ነጭ አልማዝ’ የሚባለው ጌጣጌጥ ገና ፖሊስ በእጁ ማስገባት አልቻለም። 

ባለሥልጣናት እነዚህን ጌጣጌጦች እንዴት ማስመለስ እንደቻሉ ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። 

በጥር ወር የጀመረው የተጠርጣሪዎቹ የፍርድ ሂደት ጀርመናዊያን በጉጉት እየተከታተሉት ሲሆን ችሎቱ የሚቀጥለው ማክሰኞ እንደሚቀጥል ኤኤፍፒ ዘግቧል። 

ግሪን ቮልት ስብሰቦች በቀድሞው የንጉሣዊያን ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበር ተቀምጠው ለሕዝብ ይታዩ የነበረው።

በድምሩ 3ሺህ ጌጣጌጦች ይገኙ ነበር። 

ይህ ቤተ መንግሥት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በከፊል ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ታድሶ ነው በድጋሚ ወደ ሥራ የተመለሰው። 

እነዚህን ሦስት ሺህ ውድ ጌጣጌጦች የሰበሰበው የ18ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ልዑል የነበረው አውጉስተስ ዘ ስትሮንግ ነበር። 

ልዑል አውጉስተስ የጀመርንን ቄሳርን መምረጥ ከሚችሉ ጥቂት ሉዓላን መካከል አንዱ ነበር። 

ይኸው ልዑል በኋላ ላይ የፖላንድ ንጉሥ መሆን ችሎ ነበር። 

አሁን የተመለሱት ውድ ጌጣጌጦች በዘራፊዎቹ ቀልጠው በአዲስ መልክ ይሸጣሉ የሚል ስጋት በስፋት ስለነበረ አሁን በጥሩ ይዞታ መመለሳቸው በጀርመን የቅርስ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ዘንድ ፈንጠዚያን ፈጥሯል።