የኢራን ባለሥልጣናት የወሲብ ቪድዮ ስለተለቀቀባቸው የእስልምና መርሆ አስተማሪ የምናውቀው ነገር የለም አሉ

የአራን ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ኢራን ውስጥ አንድ የእስልምና ትምህርት አስተማሪ እና ባለስልጣን የሆኑ ሰው የወሲብ ቪድዮ መለቀቁን ተከትሎ ከሥልጣናቸው ተነሱ።

የኢራን ባለሥልጣናት ስለግለሰቡ ተግባር የሚያውቁት ነገር እንደለሌ ገልጠዋል።

አንድ በይነ መረብ ላይ የተለጠፈ ቪድዮ በጊላን ግዛት የባሕልና እስላማዊ መርሆ ኃላፊ የሆኑት ሬዛ ፃጋቲ ከአንድ ወንድ ጋር ወሲብ ሲፈፅሙ አሳይቷል።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚታዩት ግለሰቦች ማንነትና የምስሉ ትክክለኛነት አልተረጋገጠም።

ሬዛ ፃጋቲ ከሥልጣናቸው ተነስተው ምርምራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ተሰምቷል።

ኢራን ውስጥ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት በሕግ የሚያስቀጣ ሲሆን ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ለተለያዩ ጥቃቶች ይጋለጣሉ።

በኃይማኖቲ አስተምህሮ እና በሒጃብ ላይ ያተኮረ ማዕከል መሥራች የሆኑት ግለሰብ ቪድዮ በማሕበራዊ ሚድያ በሰፊው የተሰራጨ ሲሆን መነጋገሪያም ሆነዋል።

ቅዳሜ ዕለት የኢራን ባህል ሚኒስትር ሞሐመድ መሕዲ ኢስማይሊ ቪድዮው ከመውጣቱ በፊት ስለግለሰቡ ምንም ዓይነት አሉታዊ ነገር ተሰምቶ እንደማያውቅ ተናግረዋል።

አንዳንድ ሰዎች ግለሰቡ ከቪድዮው መሰራጨት በኋላ ከሥልጣናቸው መነሳታቸው ምን ያክል ባለሥልጣናት እንደሚጠበቁና በአንጻሩ ደግሞ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ሆነው ለእስልምና ሕግጋት የማይገዙ ሰዎች ጥቃት እንደሚደርስባቸው ማሳያ ነው ይላሉ።

የግለሰቡ ቪድዮ በበይነ መረብ ከተሰራጨ በኋላ የኢራን ባለሥልጣናት መጀመሪያ ዝምታን መርጠው ነበር።

ነገር ግን ሐምሌ 22 የጊላን ግዛት ባሕልና የእስልምና መርሆ ክፍል የግለሰቡን ድርጊት በተመለከተ መግለጫ አወጣ።

በመግለጫው ጉዳዩ “ጥንቃቄ ለተሞላበት ምርመራ ወደ ከፍተኛ ፍትሕ ባለሥልጣናት ተልኳል” ያለ ሲሆን ቪድዮው “የእስልምና አቢዮት ግንባር የሆነውን የተከበረውን የእስልምና ባሕል እንዳያዳክመው” ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ቪድዮ መጀመሪያ በቴሌግራም ገፅ የተለጠፈው ፀረ-ተቋም በሆነው ራዲዮ ጊላን ነው።

የራዲዮ ዋና አዘጋጅ ፔይማን ቤህቡዲ ጣቢያው “የአገዛዙን ሙሰኛ ባለሥልጣናትን ድርጊት” ማጋለጡን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በሸሪያ የሚመራው የኢራን ሕግ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት በሞት ሊያስቀጣ የሚችል ወንጀል ነው ይላል።

ምንም እንኳ በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነታቸው በሞት የተቀጡ ሰዎች ብዙ ባይሆንም ብዙዎች በየቀኑ መገለል ይደርስባቸዋል።

አልፎም ሒጃብ የማይከናነቡ ኢራናዊያን ሴቶች ከፍተኛ ቅጣት ይደርስባቸዋል።

ባለፈው መስከረም ሒጃብ መከናነብ ግዴታ እንዲሆን መደረጉን ተከትሎ በመላው የሃገሪቱ ክፍል ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር።

ተቃውሞ የተቀጣጠለው የ22 ዓመቷ ማሕሳ አሚኒ ሒጃብ ባለመልበሷ ታሥራ በኢራን ግብረ-ገብነት ፖሊስ እጅ ሳለች መመቷን ተከትሎ ነው።