ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዋነኛው የናይጄሪያ አየር ማረፊያ የአውሮፕላኖች መንደርደሪያ መንገድ መብራት ተሰረቀ
በርካታ መንደኞችን በሚያስተናግደው የናይጄሪያ አየር ማረፊያ የአውሮፕላኖች መንደርደሪያ መንገድ የመብራት ስርዓት እንደተዘረፈ አንድ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገለጹ።
የጠፋውን የመብራት ሥርዓት ለማስመለስ እና ወንጀለኞችን አድኖ ለመያዝ ምርመራ እየተደረ መሆኑንም የኤየርፖርት ባለስልጣን ቃል አቀባይ ያኩቡ ፉንቱዋ ገልጸዋል።
ሌጎስ ውስጥ በሚገኘው ሙርታላ ሙሃመድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ስርቆቱ መቼ እንደተፈጸመ የሚታወቅ ነገር የለም።
የአካባቢው ብዙሃን መገናኛዎች እንደዘገቡት ከሆነ ግን በዝርፊያው የአየር መንዱ ሰራተኞች ሳይሳተፉ አልቀረም።
የአውሮፕላን ማረፊያው መሬት ላይ የተገጠመው የመብራት ሥርዓት ባለፈው ኅዳር ወር ነበር አገልግሎት መስጠት የጀመረው።
አውሮፕላኖች ለማረፍ እና ለመነሳት በሚንደረደሩበት መንግድ ላይ የሚገጠሙት መብራቶች በምሽት እና እይታን በሚጋርድ የአየር ጸባይ ወቅት አብራሪዎች መንገድ እንዳይስቱ ይጠቁማሉ።
አሁን በተፈጸመው ስርቆት ምክንያት አውሮፕላኖች በሌላው የአየር ማረፊያው መንደርደሪያ መንገድ ላይ ለማረፍ በመገደዳቸው በዓለም አቀፍ በረራዎች ላይ መስተጓጎልን ፈጥሯል።
ስርቆቱን ተከትሎ የናይጄሪያ የፌዴራል ኤርፖርት ባለስልጣን በቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮችን ለመከላከል አንዳንድ ክልከላዎችን ደንግጓል።
ሌቦቹ እንደመልካም አጋጣሚ የተጠቀሙት የመብራት ሥርዓት የተዘረጋበት የአውሮፕላን ማረፊያው ክፍል ለጥገና በሚል ለተወሰኑ ጊዜያት ዝግ ሆኖ መቆየቱን መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ምንጮቹ እንደሚሉት ስርቆቱ ከአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ በሚሰሩ ሰራተኞችና ከውጭ በሚገቡ ሌቦች የጋራ ትብብር የተፈጸመ ነው።