የሱተን የመጀመሪያ ሳምንት ግጥሚያ ግምት፡ዩናይትድ አቻ ይወጣል፣ አርሰናል ያሸንፋል

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2024/25 ውድድር ዓመት ዛሬ ምሽት ይጀምራል።

ኦልድትራፎርድ ላይ ማንቸስተር ዩናይትድ ከፉልሃም በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ የውድድር ዓመቱ ይጀመራል።

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ የዘንድሮውን የሊጉን ጨዋታዎች ግምትም በየሳምንቱ ያቀርባል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ፉልሃም

የመጀመሪያውን ሳምንት ጨዋታዎች ግምት መገመት ከባድ ነው። ጨዋታውን ማንቸስተር ያሸንፋል ብዬ አላስብም።

ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ዎልቭስን ቢያሸንፉም አሳማኝ አልነበሩም።

ባለፈው ዓመት ኦልድትራፎርድ ላይ ያሸነፉት ፉልሃሞች በርካታ ተጫዋቾቻቸው ወደ ሌላ ክለብ አቅንተዋል።

ፉልሃም ከጨዋታው አንድ ነገር የሚያገኝ ይመስለኛል።

ግምት፡ 1 – 1

ቅዳሜ

ኢፕስዊች ከ ሊቨርፑል

የኢፕስዊቹ አሰልጣኝ ኪዬረን ማክኬና በተከታታይ ሁለት ውድድር ዓመታት ክለቡን ከሊግ አንድ ወደ ፕሪሚርሊጉ በማሳደጋቸው አድናቆቴ ከፍተኛ ነው።

የውድድር ዓመቱን የሚጀምሩበት መንገድ ወሳኝ ነው። ቡድኑ ከሊቨርፑል ጋር ውድድሩን መጀመሩ ደግሞ ፈተናውን ከባድ ያደርገዋል።

ሊቨርፑል አዲስ ተጫዋች ባያስፈርምም አሰልጣኝ አርን ስሎት የፊት መስመራቸው ጠንካራ ከመሆኑም በላይ ኢፕስዊች የሚቋቋመው አይመስልም።

ኢፕስዊቾች ሳቢ አጨዋወትን ከመምረጣቸውም በላይ ጎል እንደሚያስቆጥሩ ብጠብቅም በዚህ ጨዋታ ግን ነጥብ አያገኙም።

ግምት፡ 1 – 3

አርሰናል ከ ዎልቭስ

ብዙዎች አርሰናል የሊጉን ዋንጫ ያነሳል ለምን እንደሚሉ ባውቅም ይህ ግን የሚወሰነው በማንቸስተር ሲቲ መዳከም ላይ ነው።

የማይክል አርቴታ ቡድን ያለፈውን ዓመት ዓይነት የሊግ ፉክክር ለማስቀጠል በጥሩ ውጤት የውድድር ዓመቱን መጀመር አለባቸው።

ዎልቭስ መጨረሻ አካባቢ እየተዳከመ ቢመጣም በአሰልጣኝ ጋሪ ኦኒዬል ስር ድንቅ ጉዞ ማድረግ ችለው ነበር።

እንደፔድሮ ኔቶ እና ማክስ ኪልማን ያሉ ተጫዋቾችን መተካት የግድ ይላቸዋል። ይህን ጨዋታ መድፈኞቹ ያሸንፋሉ።

ግምት፡ 2 – 0

ኤቨርተን ከ ብራይተን

ይህ አዲሱ የብራይተን አሰልጣኝ ፋቢያን ሃርዝለር አዲስ አጨዋወት ይዘው ስለመምጣታቸው ሁሉም የሚመለከትበት አጋጣሚ ነው።

ኤቨርተኖች በአሰልጣኝ ሾን ዳይሽ ስር በፈተና ውስጥ ማለፍን ለምደዋል።

ባለፈው ዓመት የነጥብ ቅነሳ ባይደረግባቸው በሊጉ ሰንጠረዥ አጋማሽ ላይ ይጨርሱ ነበር። ዘንድሮም ተመሳሳይ እንደሚሆን አስባለሁ።

ኤቨርተኖች ይህንን የውድድር ዓመት በድል ይጀምራሉ።

ግምት፡ 1 – 0

ኒውካስል ከ ሳውዝሃምፕተን

ይህ ጨዋታ ከታች ለመጣው ሳውዝሃምፕተን ከባድ ጅማሮ ነው።

ኒውካስሎች ካላቸው ድንቅ ተጫዋቾች በተጨማሪ ጉልበት ያላቸው እና የማይደክሙ ተጫዋቾችንም ይዘዋል።

ሳውዝሃምፕተኖች ከፊታቸው ምን እንዳለ ቢያውቁም መቋቋም ግን አይችሉም። ኒውካስል ይህን ጨዋታ በሰፊ የግብ ልዩነት ያሸንፋል።

ግምት፡ 3 – 0

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ቦርንመዝ

ቦርንመዝ አጥቂውን ዶምኒክ ሶላንኬን ለመተካት ብራዚላዊውን ኤቫኒልሰንን ከፖርቶ አስፈርሞ ደጋፊዎችን አስፈንድቋል።

ካለፉት ዓመታት ዝውውር መሰኮት አንጻር በፎረስት ቤት የሚገቡ እና የሚወጡ ተጫዋቾች ቁጥር አነስተኛ ነው።

ባለፈው ኣመት ሁለቱ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ ቦርንመዝ ባለቀ ሰዓት ባስቆጠራት ጎል 3 ለ 2 አሸንፏል።

ይህ ጨዋታ ብዙም ሳቢ ነገሮች የሚታዩበት እንደማይሆን ብገምትም ፎረስት በጠባብ ውጤት ያሸንፋል ብዬ አስባለሁ።

ግምት፡ 2 – 1

ዌስት ሃም ከ አስቶን ቪላ

ዌስት ሃም በክረምቱ የዝውውር መስኮት ጥሩ ተንቀሳቅሷል።

በአዲሱ አሰልጣኝ ዩሊየን ሎፕቴጉ ስር ወደ ‘ዌስት ሃም የአጨዋወት መስመር’ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።

አስቶን ቪላ እንዳለፈው ዓመት እስከ አራት ያለውን ደረጃ ለማግኘት ከባድ ሊሆንበት ይችላል። ሻምፒዮንስ ሊግ ሲጀመር ደግሞ መንገዶቹ አልጋ በአልጋ አይሆኑም።

ሁለቱም ቡድኖች የሚያሽንፉበት ምክንያት በመኖሩ ለመገመት ከባድ ነው። በመሆኑም አቻ ይወጣሉ እላለሁ።

ግምት፡ 1 – 1

እሑድ

ብሬንትፎርድ ከ ክሪስታል ፓላስ

አጥቂው አይቫን ቶኒ አሁንም በብሬንትፎርድ ቤት ይቀጥላል። ቡድኑ ያለ ተጫዋቹ ብዙ በማሳለፉ ቶኒ ከብሬንትፎርድ ቢለቅ ቡድኑ ላይ የጎላ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም።

ባለፈው ዓመት ፓላሶች በአሰልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ስር ያሳዩትን ድንቅ አቋም ይደግማሉ ብዬ አላስብም።

ዢን-ፊሊፔ ማቴታ ኦሎምፒክ ላይ በመሳተፉ ለጨዋታው ላይደርስ ይችላል። ማይክል ኦሊሴ ክለቡን ለቋል። ማክር ጉሂ እና ሦአኪም አንደርሰንም ሊለቁ ይችላሉ።

ሁለቱ ቡድኖች እንዴት ተደራጅተው እንደሚገቡ ማየት የሚያስፈልግ ሲሆን ጨዋታው በአቻ ውጤት እንደሚጠናቀቅ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 – 1

ቼልሲ ከ ማንቸስተር ሲቲ

እረፍታቸው ዘግይቶ በመጠናቀቁ ምክንያት በርካታ ማንቸስተር ሲቲ ከዋክብት በዚህ ጨዋታ ላይሰለፉ ይችላሉ።

ከቼልሲ ምን መጠበቅ እንዳለብኝም ሆነ ክለቡ ምን መሥራት እንዳሰበ ለማወቅ ይከብደኛል።

ቡድኑ ዋንጫ የሚያነሳ ቡድን እየገነባ ነው ወይስ ሌላ ዓላማ አለው?

ቼልሲ ባለተሰጥኦ ያላቸውን ተጫዋቾች ይዟል። ኮል ፓልመርም ከቀድሞ ከክለቡ ጋር ይገናኛል። ጨዋታውን ግን ሲቲ የሚያሽነፍ ይመስለኛል።

ግምት፡ 1 – 2

ሰኞ

ሌስተር ከ ቶተንሃም

አሰልጣኝ አንጅ ፖስትኮግሉ በሁለተኛ ውድድር ዓመታቸው ጫና ውስጥ ናቸው ብዬ አላሰብም።

አሰልጣኙ ለውጥ በማምጣታቸው ጉዳይ ማንም ጥያቄ አያነሳም። ስለዚህ የምን ጫና ነው? ትክክል ባይሆንም ሰዎች እንዳይሳካላቸው የሚፈልጉ ይመስለኛል።

አሰልጣኙም በዚህ ዓይነት ጫና ስር ማለፍ ልምድ ስላላቸው የሚጨነቁ አይመስለኝም።

ሶላንኬን ማስፈረማቸው ጨምሮ ቡድኑ የተሻለ የውድድር ዓመት እንደሚያሳልፍ እገምታለሁ።

ሌስተር በአሰልጣኝ ስቲቭ ኩፐር ስር የተደራጀ ቡድን ይሆናል። ወደ ሊጉ ከመጡ ሦስት ቡድኖችም በሊጉ የመቆየት ዕድል አለው። ይህንን ጨዋታ ግን የሚያሸንፋው ቶተንሃም ነው።

ግምት፡ 1 - 3