ዩክሬን በሩሲያ ግዛት የወታደራዊ አስተዳደር ቢሮ አቋቋመች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩክሬን በሩሲያ ግዛት የወታደራዊ አስተዳደር ቢሮ አቋቋመች። ቢሮው የተከፈተው በምዕራብ ኩርስክ ክልል ነው።

ዩክሬን ወደዚህ የሩሲያ ግዛት ፍጹም ያልተጠበቀ ዘመቻ አድርጋ ወደ ሩሲያ ድንበር ዘልቃ ሰፊ ቦታ መያዟ አይዘነጋም።

ጄኔራል ሲሪስኪ የተባሉ አንድ የዩክሬን ጦር ከፍተኛ መኮንን ይህ ቢሮ በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች “ሕግና ሥርዓትን” የሚያስከብር ይሆናል ብለዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር አንድሬ ቤሎሶቭ በበኩላቸው በዚያ ያሉ ዜጎቻችንን ለመታደግ ኃይል እንልካለን ብለዋል።

ዩክሬን ትናንት ሐሙስ ሌሎች የሩሲያ መንደሮችን መቆጣጠሯን ይፋ አድርጋለች። አሁን ከድንበር ወደ ሩሲያ ግዛት 35 ኪሎ ሜትር ዘልቃ የገባች ሲሆን 1ሺህ 150 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ግዛት መቆጣጠር ችላለች።

አሁን ዩክሬን በድምሩ 82 መኖሪያ መንደሮችን ተቆጣጥራለች ሲሉ ጄኔራል ሲሪስኪ ተናግረዋል።

ኪየቭ የሩሲያ ግዛቶችን እጇ አስገብቶ የማቆየት ፍላጎት የላትም ብለዋል ጄኔራሉ።

አሁን የሩሲያ ግዛትን ገፍቶ መግባት ያስፈለገው ሞስኮ ላይ ጫና ለመፍጠር ነው ብለዋል የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄዮሪህ ቴኪ።

ሩሲያ የተቃጣባትን ጥቃት አስመልክቶ መልሶ ማጥቃት ለመሰንዘር ዝግጅት ላይ ናት ተብሏል።

በዚህ እቅድ ላይ ከኩርስ ሌላ ዩክሬን ድንበር ላይ ያሉ ክልሎችም ተካተዋል።

ሩሲያ በቤልጎሮድ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች። ሰኞ ዕለት 11ሺህ ሰዎች ከቤልጎሮድ አካባቢ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ ተደርገዋል።

ሩሲያ ከዚህ ባሻገር በዩክሬን ከተወሰዱ የኩርስክ ግዛቶች የተወኑትን ማስመለስ መቻሏን እየተናገረች ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ የዩኬ ምንጮች ለቢቢሲ እንደገለጹት ዩናይትድ ኪንግደም ለዩክሬን የሰጠቻት ዘመናዊ ታንኮች ዩክሬን የሩሲያ ግዛቶችን ለመያዝ እንድትጠቀመው ፈቅዳለች።

ዩኬ ለዩክሬን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ካስታጠቁ የአውሮፓ አገሮች የመጀመርያ ናት። ቻሌንጀር-2 የተሰኙ ዘመናዊ ታንኮች ባለፉት ሁለት ዓመታት ተበርክተዋል። ይሁንና እነዚህን መሣሪያዎች በራሷ ግዛት ራሷን ለመከላከል እንጂ በሩሲያ ግዛት እንድትጠቀማቸው አልተፈቀዱላትም ነበር።

ዩክሬን በአሜሪካና ጀርመን የተለገሷትን ሌሎች የጦር መሣሪያዎችም እየተጠቀመችባቸው ትገኛለች።

እነዚህ አገሮች ይህን ልዩ ፍቃድ በተመለከተ ተቃውሞ ያላቀረቡ ሲሆን በቅርቡ ዩክሬን ባደረገችው ዘመቻ ግን እምብዛም መረጃው እንዳልነበራቸው ነው የተነገረው።

አሁንም ቢሆን በምዕራባዊያን ዘንድ በዩክሬን ያልተጠበቀ ግስጋሴ ዙርያ መደነቅ ቢኖርም ፑቲን ከዚህ ቀጥሎ ምን እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ በብርቱ ሳያሳስባቸው አልቀረም።

ፑቲን ምዕራባዊያን ዩክሬንን በታንክ እንዳያስታጥቁ በተደጋጋሚ አሳስበው የነበረ ሲሆን ምዕራባዊያን ግን ማስጠንቀቂያውን ቸል ብለውታል።

አሁን ኪየቭ በእርዳታ ካገኘቻቸው መሣሪያዎች በሩሲያ ግዛት እንዳትጠቀመው ገደብ የተጣለባት የረዥም ርቀት ተመዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ብቻ ነው።

ዜሌንስኪ ግን ምዕራባዊያን ይህን በረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ዙርያ ያስቀመጡባትን ገደብ እንዲያነሱላት ጥያቄ ማቅረቧን አላቋረጠችም።