የጀርመኑ መሪ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ለሩሲያ መሰለፋቸው ጦርነቱን እንደሚያባብስ ለፑቲን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Steffen Kugler/BPA/Handout via Reuters
የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ሩሲያ የሰሜን ኮሪያን ወታደሮች በዩክሬን ማሰማራቷ ግጭቱን በከፋ ሁኔታ ያባብሰዋል ሲሉ ለሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን መናገራቸውን የመንግሥት ምንጮች ገለጹ።
ሾልዝ ይህን ያሉት ሁለቱ መሪዎች በሁለት ዓመታት ውስጥ አርብ ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የስልክ ንግግራቸው ወቅት ነው።
ሾልዝ፣ ፑቲን ጦርነቱን እንዲያስቆሙ እና የሩሲያን ወታደሮች ከዩክሬን እንዲያስወጡም ጠይቀዋል።
ክሬሚሊንም ሁለቱ መሪዎች ያደረጉትን ንግግር “ በዩክሬን ስላለው ሁኔታ የተደረገ ዝርዝር እና እውነተኛ የሃሳብ ልውውጥ” ያለው ሲሆን ንግግሩም አዎንታዊ ነበር ብሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ በበኩላቸው የቀረበውን ጥሪ ብዙ ውስብስብ ነገሮችን የሚያመጣ እና የፑቲንን ለብቻ መቆም የሚያዳክም ነው ብለውታል።
እንደ የመንግሥት ምንጮች ከሆነ መራሔ መንግሥቱ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን ፍትሐዊ እና ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲመጣ ሞስኮ ከኪዬቭ ጋር ድርድር እንዲታካሂድ ጠይቀዋል።
ሾልዝ ጨምረውም አገራቸው ጀርመን ዩክሬን የሩሲያን ቁጣ ለመከላከል የምታደርገውን ትግል አስፈላጊ እስከሆነ ጊዜ ድረስ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን አስረግጠዋል።
ሾልዝ ሩሲያ በተለይ ሰላማዊ ነዋሪዎች በሚገለገሉባቸው መሠረተ ልማቶች ላይ የምትፈፅመውን የአየር ጥቃት አውግዘዋል።
ለአንድ ሰዓት ገደማ በቆየው የስልክ ንግግራቸው ሁለቱ መሪዎች ንግግራቸውን ለመቀጠልም ተስማምተዋል። የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን የስልክ ንግግሩ ጥያቄ የቀረበው በጀርመን እንደነበር ዘግበዋል።
የጀርመን መንግሥት፣ በርሊን በዩክሬን ራስ ላይ ሆኖ ከሞስኮ ጋር ስምምነት ለመመስረት እየሞከረ ነው ከሚለው ውንጀላ በተለይም በ20ኛው ክፍለ ዘመን በምሥራቅ አውሮፓ በናዚ ጀርመን እና በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት መካከል የነበረውን አሳዛኝ ትዝታዎች ከግምት በማስገባት የሚቀርብበትን ውንጀላ ማስወገድ ይፈልጋል።
የመራሔ መንግሥቱ ጽሕፈት ቤት ባወጣው የጽሑፍ መግለጫም ሾልዝ ከፑቲን ጋር ከመነጋገራቸው በፊት ከዘሌንሰኪ ጋር መነጋገራቸውን ጠቁሟል።
ሾልዝ ከፑቲን ጋር ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማውራት ከዘሌንስኪ ጋር በድጋሜ ለመነጋጋርም አቅደዋል።
ክሬሚሊን ለሩሲያ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫም፣ ፑቲን ከሾልዝ ጋር ባደረጉት ንግግር፣ የሩሲያ እና ጀርመን ግንኙነት በጀርመን ባለሥልጣናት “ ወዳጅነት በጎደለው አካሄድ ‘ የተነሳ ታይቶ የማይታወቅ ውርደት ገጥሞታል ብለዋል።
እንደ ክሬሚሊን ከሆነም ማንኛውም ሊካሄድ የሚችል የሰላም ስምምነት አዲስ ባለው የግዛት ሁኔታ ሩሲያ ከ2022 ጀምሮ የተቆጣጣረችው የዩክሬን ግዛት] ላይ መመስረት እንዳለበት ፑቲን ለሾልዝ አስረድተዋል።
ፑቲን ጨምረውም ሰላም መምጣት የሚችለው የግጭቱን ምክንያት ከሥሩ በማድረቅ ነው ብለዋል።
ክሬሚሊን በዩክሬን ላይ ወረራ የፈፀመችው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በምሥራቃዊ አውሮፓ በመስፋፋቱ እንደሆነ ትገልጻለች።
በስልክ ንግግራቸውም አሁን ላይ የተከሰተው ቀውስ ኔቶ በዩክሬን ግዛት ፀረ ሩሲያ ብርጌድ ለመፍጠር ያለመውና ለአንድ ዓመት የዘለቀው ፖሊሲ ውጤት መሆኑን ፑቲን መናገራቸው ተዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት የጀርመን ቴሌቪዥን ከሾልዝ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ኦልዝ ፑቲን ወደ ሰላም ንግግር እንዲመጡ ለመገፋፋት ከፑቲን ጋር ለመነጋገር እቅድ እንደነበራቸው ተናግረው ነበር።
ሾልዝ ይህንን የሚያደርጉት እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ከሌሎችም ጋር በመመካከር መሆኑንም ተናግረዋል።
ሾልዝ በሚቀጥለው ሳምንት በሪዮ ዲ ጀኔሮ በሚካሄደው የቡድን 20 አገራት ስብሰባ ወቅትም በዩክሬን ስላለው ጦርነት የሩሲያ ደጋፊ ከሆኑት ከቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ለማውራት እቅድ እንዳላቸውም ጭምጭምታዎች አሉ።
ሾልዝ ከፑቲን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ በስልክ የተነጋገሩት ከሁለት ዓመት በፊት ታኅሳስ ወር ላይ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የተገናኙትም በዩክሬን ላይ ሰፊ ወረራ ከመፈፀሙ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Kremlin Press Office/Anadolu Agency via Getty Images
በወቅቱም ሩሲያ ዩክሬንን የመውረር ፍላጎት እንደሌላት በፑቲን ቃል ተገብቶላቸው ነበር ወደ በርሊን የተመለሱት ። ሆኖም ከሳምንት በኋላ ወረራው በመፈፀሙ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው እምነት ተሰብሯል።
ለአስርተ ዓመታት በርሊን በንግድ እና በኃይል በመተሳሳር ከሞስኮ ጋር ሰላም ለማረጋጋጥ ሞክራለች። ይህንን ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያላቸው ፍላጎት ግን ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈፀመች በኋላ አክትሟል።
አሁን ላይ ጀርመን ለዩክሬን የጦር እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ከአሜሪካ እና ከሌሎች አጋሮቿ በመቀጠል ሰፊ ድጋፍ የምታደርግ አገር ሆናለች።
ሆኖም ከወራት በኋላ የሚካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም የሚደረጉ ግፊቶች ጨምረዋል።
ቀኝ አክራሪው ኤኤፍዲ እና ግራ ዘመሙ ቢኤስደብሊው መንግሥት ሰላም ለማምጣት የሚጠበቅበትን ባለመወጣቱ ይከሳሉ።
የሾልዝ የጥምር መንግሥት ባለፈው ሳምንት የፈረሰ ሲሆን እስከ ምርጫው ድረስ በውስን አስተዳደር እየመሩ ይቆያሉ። እርሳቸውና ፓርቲያቸውም በምርጫው ላይ ብዙ ውጤት አላሳዩም።
ጀርመን በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በፖለቲካውም ሆነ በምጣኔ ሐብቱ ክፉኛ ተመታለች። በመሆኑም ሾልዝ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያደርጉት ማንኛውም ጥረት በምርጫው ወቅት ያላቸውን እድል ሊወስነው ይችላል።












