የትራምፕ አስተዳደር በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን እንጂ በሩሲያ የተያዙ ግዛቶች እንዲመለሱ አይሰራም

የፎቶው ባለመብት, EPA
አዲሱ አስተዳደር በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን እንጂ በሩሲያ የተያዙ ግዛቶች እንደሚለሱ እንደማይሰራ የተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ አማካሪ ተናግረዋል።
በትራምፕ የ2024 የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባል ሆነው ያገለገሉት ብራያን ላንዛ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን የሚጠይቋቸው “ሰላም እንዲሰፍን” ነው።
“ዜሌንስኪ ወደ ጠረጴዛው መጥተው ሰላም የምናገኘው ክሬሚያን ስናስመልስ ብቻ ነው ካሉን ጉዳዩን ከቁም ነገር አልያዙትም ማለት ነው፤ ክሬሚያ ሄዳለች።”
የትራምፕ ቃል አቀባይ የሆኑ ግለሰብ ግን ብራያን ላንዛ የሰጡት አስተያየት “የተመራጩ ፕሬዝደንትን ሐሳብ አይወክልም” ብለዋል።
ሩሲያ ክሬሚያን በአውሮፓውያኑ 2014 ነው ከዩክሬን የገነጠለችው። ከ8 ዓመታት በኋላ ደግሞ ዩክሬን ላይ ወረራ በመፈፀም በምስራቃዊው የሀገሪቱ ክፍል በርካታ ግዛቶችን ተቆጣጥራለች።
ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ዋነኛ ትኩረታቸው ጦርነቱን ማስቆም እንደሆነ ይናገራሉ። ለጦርነቱ አሜሪካ የምትልከው ወታደራዊ እርዳታ ተገቢ አይደለም የሚልም አቋም አላቸው።
ነገር ግን ትራምፕ በዩክሬን እንዴት ሰላም ሊያሰፍኑ እንዳሰቡ ያሉት ነገር የለም።
በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ 2016 እና 2024 የተሳኣተፉት ላንዛ ምስራቅ ዩክሬን የሚገኙ ግዛቶችን በተለመከተ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። ነገር ግን ክሬሚያን ከሩሲያ ማስመለስ የማይታሰብ ነው በማለት ይህ “የአሜሪካ ዓላማ አይደለም” ብለዋል።
“ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ክሬሚያን ማስመለስ ከሆነ እና ይህን ለማድረግ ደግሞ የአሜሪካ ወታደሮች ለመጠቀም ካሰቡ ይህ የማይሆን ነው እንላለን።”
አሜሪካዊያን ወታደሮች በዩክሬን ጦርነት ላይ ተሳትፈው አያውቁም። ዩክሬንም የአሜሪካ ወታደሮች ከሩሲያ ጋር በሚደረገው ጦርነት የአሜሪካ ወታደሮች እንዲሳተፉ ጠይቃ አታውቅም። እሳቸው እንደሚሉት አሜሪካ ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ “ሰላም እና ግድያን ማስቆም” ነው።
“የማሸነፍ ዓላማ ሳይሆን የሰላማ ዓለማ ነው ያነገብነው። በዚህ ጉዳይ ግልፅ የሆነ ውይይት ማድረግ ይጠበቅብናል” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለቀድሞው የትራምፕ አማካሪ አስተያየት ምላሽ የሰጡት የዜሌንስኪ አማካሪ የሆኑት ዲሚትሮ ሊትቪን እንደሚሉት ሰላም እንዲመጣ ጫና ማደር ያለበት “ጦርነት የሚፈልጉት ፑቲን ላይ እንጂ” ዩክሬን ላይ መሆን የለበትም።
“ፑቲን በጦርነቱ ብዙ ሰዎችን እየፈጀ ነው። ይህ ምንን ያሳየናል? ጦርነቱ እንዲቀጥል እንደሚፈልግ ግልፅ ማሳያ ነው” ይላሉ።
ትራምፕ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ወደ ሥልጣን ይመጣሉ። በዩክሬን ሰላም የሚመጣበት መንገድ ላይ ከአማካሪዎቻቸው ጋር ይመክራሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ስማቸው ያልተጠቀሰ የቀድሞው የትራምፕ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ “ፕሬዝደንቱ ብሔራዊ ደኅንነትን በተለመከተ የራሳቸውን አቋም ነው የሚያራምዱት” ሲሉ ለዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ተናግረዋል።
ትራምፕ ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ከዜሌንስኪ ጋር የስልክ ልውውጥ ያደረጉ ሲሆን ቢሊየነሩ ኢላን መስክ አብሮ እንደነበር ተነግሯል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቢሮ የቅርብ ሰዎች ዜሌንስኪ እና ትራምፕ “ግማሽ ሰዓት የፈጀ ውይይት” ማድረጋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የትራምፕ ተቃዋሚ የሆኑት የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ተመራጩ ፕሬዝደንት ለሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የሚያሳዩት አቋም የተለሳለሰ ነው ሲሉ ይወቅሷቸዋል። በዩክሬን ስላለው ጦርነት ያላቸው አቋምም ዩክሬን እጇን እንድትሰጥ የሚያደርግና ለአውሮፓ አደጋ ያለው ነው ይላሉ።
የኢስቶኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስተን ሚካል ዩክሬን የምታፈገፍግ ከሆነ “ሩሲያ የበለጠ የመግፋት ፍላጎቷ ይጨምራል” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ባለፈው ሳወር ለዩክሬን ፓርላማ “የድል ዕቅድ” ያቀረቡት ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ የዩክሬንን ግዛት ቅንጣት ታክል አሳልፈው እንደማይሰጡ እና የግዛት ሉዐላዊነቷንም እንደሚያስጠበቁ ተናግረዋል።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት “በአንድ ቀን” እንደሚያስቆሙት ቢናገሩም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የትራምፕ የቀድሞ አማካሪዎች ባለፈው ግንቦት በፃፉት አንድ ፅሑፍ አሜሪካ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ እርዳታ ማድረጓን የምትቀጥለው ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የሰላም ስምምነት ከፈፀመች ነው ይላል።
ፑቲን ለትራምፕ በላኩት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት በዩክሬን ያለው ጦርነት እንዲቆም ትራምፕ ያቀረቡት ሐሳብ “ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል።
የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጥቂት ወራት በፊት ለዩክሬን 61 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ወታደራዊ እርዳታ ማፅደቁ ይታወሳል።












