ትራምፕ አሜሪካ ወደ ገሃነም ትገባለች አሉ

ታትሟል

መረጃዎችን ለመደበቅ የንግድ መዝገቦችን አጭበርብረዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ወደ ገሃነም ትገባለች ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው በድፍረት ተናግረዋል።

ትራምፕ ማክሰኞ፣ መጋቢት 26/2015 በዋለው ችሎትም በሰጡት የምስክርነት ቃል ጥፋተኛ አይደለሁም ብለዋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መዘገቦችን አጭበረበሩ የተባለው ለአውሮፓውያኑ 2016 ምርጫ እየተሰናዱ በነበረበት ወቅት ነው።

ትራምፕ በኒውዮርክ በሚገኘው የማንሃተን ፍርድ ቤት 34 ክሶች ቀርቦባቸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት በተወዳደሩበት ዋዜማ ከወሲብ ተዋናይት ስቶርሚ ጋር ምሥጢር አታውጪብኝ በሚል ከፈሉት በተባለው ገንዘብ እና ገንዘቡን ለማወራረድ ያቀረቡት ምክንያት ለዚህ የወንጀል ክስ ዳርጓቸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ በወንጀል የተከሰሱ የመጀመርያው ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

“የፈጸምኩት ብቸኛው ወንጀል አገራችንን ለማፍረስ እየጣሩ ካሉ ኃይሎች መከላከሌ ነው” ሲሉ የ76 ዓመቱ ትራምፕ ከፍርድ ቤት መልስ ፍሎሪዳ በሚገኘው ማር አ ላጎ መኖሪያ ቤታቸው ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት በሚቀጥለው ዓመት አገሪቷ በምታካሂደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ጣልቃ ለመግባት በዲሞክራቲክ ፓርቲ የተቀነባበረ የሴራ አካል ነው ሲሉም ክሱ ሃሰተኛ ነው ሲሉ አጣጥለውታል። ትራምፕ በሚቀጥለው ዓመትም በሚደረገው ምርጫ ለመወዳደር እንዳሰቡም ተገልጿል።

ለአንድ ሰዓት ያህል በነበረው የችሎት ሂደትም ምንም አይነት ቃል ያልተነፈሱት ትራምፕ ዳኛ ሁዋን መርቻን ጥፋተኛ ስለመሆን አለመሆናቸው ብቻ ሲጠይቁዋቸው ጥፋተኛ አይደለሁም ሲሉ የክስ መቃወሚያቸውን አሰምተዋል። ከፍርድ ቤትም ሲወጡ ለጋዜጠኞች ትንፍሽ ያሉት ነገር የለም።

ዶናልድ ትራምፕ በ2016 ምርጫ ወቅት እንቅፋት እንዳትሆንባቸው ለወሲብ ተዋናይት ስቶርሚ ዳኒኤልስ “ስለነበረን ነገር ትንፍሽ እንዳትይ” በሚል አፍ ማስያዣ 130ሺህ ዶላር ገንዘብ ዝውውር ያደረጉት በቀድሞ ጠበቃቸው ማይክል ኮህን በኩል ነበር።

እንዲህ ዓይነቱ ክፍያ ህገወጥ ባይሆንም ለፕሬዚዳንታዊ ዘመቻ ያግዝ ዘንድ ገንዘብ ማውጣትና ይህንንም ይፋ አለማድረግ የአገሪቱን የፌደራል የምርጫ ዘመቻ ፋይናንስ ህግን ይጥሳል።

ከትራምፕ በተቃራኒ የቆመው የቀድሞ ጠበቃቸው ኮህን ክፍያው የተፈጸመው በትራምፕ መመሪያ መሆኑን ተናግሯል።