የሐኪሟን ስህተት ለሰባት ዓመታት የደበቀው ሆስፒታል ይቅርታ ጠየቀ

ታትሟል

በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል የአንድ ቀዶ ጥገና ሐኪም ስህተትን ለሰባት ዓመታት በመደበቁ ይቅርታ ጠየቀ።

ኢስት ኬንት ሆስፒታልስ ትረስት በተባለው የሕክምና ተቋም፣ ሉዊስ ደምስተር የተባለች ሴት ስትወልድ ከፍተኛ ደም መፍሰስ ገጥሟት ነበር።

ለሰባት ዓመታት ያህል ደም መፍሰስ የገጠማት የልጇ ክብደት ከፍተኛ ስለነበረ እንደሆነ ሲነግሯት ቆይተዋል። ነገር ግን ለገጠማት የደም መፍሰስ ተጠያቂ የሆስፒታሉ ሠራተኛ የሆነች የቀዶ ሕክምና ባሙያ ነበረች።

የሐኪሟን ስህተት ለሰባት ዓመት በማድበስበሱ ሆስፒታሉ አሁን ይቅርታ ጠይቋል። ዋና ኃላፊዋ ትሬሲ ፍሌቸር “ከስህተታችን ተምረናል” ብለዋል።

የ34 ዓመቷ ሉዊስ ለቢቢሲ “በውሸታቸው ገፍተውበት ነበር” ብላለች።

የወለደችው እአአ በ2015 ሲሆን፤ የሕክምና ስህተቱ እንደተፈጠረ የታወቀው ዘንድሮ ሆስፒታሉ ባደረገው ምርመራ ነው።

የመጀመሪያ ልጇን ልትወልድ ሁለት ቀናት ሲቀሯት ነበር እናት ልዊስ የሕክምና እክል የገጠማት።

የልጇ ክብደት እንደጨመረ እና ጉበቷም እንደተጎዳ በሐኪሞች ተነግሯታል። ከወለደች በኋላ ከፍተኛ ደም ሊፈሳት እንደሚችልም ገልጸውላታል።

ዶ/ር ቢል ኪከፕ የተባሉ ባለሙያ ስለ እናቶች ሕክምና ዘንድሮ በሆስፒታሉ ላይ ምርመራ አድርገዋል።

ከ2009 እስከ 2020 በሆስፒታሉ የሞቱ 45 ጨቅላ ሕጻናት የተሻለ እንክብካቤ ቢደረግላቸው ኖሮ ይተርፉ እንደነበርም ደርሰውበታል።

“ያ ወቅት የጣለብኝ ጠባሳ እስካሁን አልሻረም”

ልጇን በቀዶ ሕክምና ከወለደች በኋላ ራሷን መሳቷን ያስተዋሉት እናቷ ነበሩ።

ቤተሰቡ ጤነኛ ልጅ በመውለዷ ደስታውን እየገለጸ ሳለ ነበር ራሷን መሳት የጀመረችው።

“እያዋራኋት ሳለ ሰውነቷ ይደክም፣ ዐይኗም ይጨፈን ጀመር። ብርድ ልብሱን ስገልጠው ልጄ ደም በደም ሆናለች” ሲሉ የ61 ዓመት ነርስ እናቷ ወቅቱን ያስታውሳሉ።

ሉዊስ ከዚያን ቀን የምታስታውሰው እናቷ እየጮሁ የእርዳታ እና የድረሱልኝ ጩኸታቸውን ሲያሰሙ ነው።

የቀዶ ሕክምና ባለሙያዋም ሉዊስ ደም እየፈሰሳት ያለው ልጅ ከወለደች በኋላ ማሕጸኗ የስፋት መጠኑ ባለመቀነሱ እንደሆነ ነገረቻት።

ደሙን ለማቆም የተደረገው ጥረት ስላልተሳካ ሉዊስ በድጋሚ ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል ተወሰደች።

የደም ልገሳ ከተደረገላት ከቀናት በኋላ ነበር ያገገመችው።

ቤተሰቦቿ ሕክምናው ሲደረግላት አንዳች ስህተት እንደተፈጸመ ስላሙ የሕክምና ሰነዶቿን ከሆስፒታሉ ተቀብለው ቢያገላብጡም የቀዶ ሕክምና ባለሙያዋ ከገለጸችላቸው የተለየ መረጃ አላገኙም።

ሆስፒታሉም ምንም ችግር አልተፈጠረም ብሎ ምርመራው ቆመ።

ሉዊስ ልጇን በሰላም በመገላገሏ ደስተኛ እንድትሆን ተነግሯት ወደ ቤቷ ብትላክም ክስተቱ ግን ከሕሊናዋ አልጠፋ አለ።

“ነገሩ የአእምሮ ጤናዬን ጎድቶታል። ሌላ ልጅ መውለድም አልቻልኩም። ያ ወቅት የጣለብኝ ጠባሳ እስካሁን አልሻረም” ትላለች።

ከሁለት ዓመት በፊት በሆስፒታሉ ምርመራ ሲደረግ ሉዊስ እና እናቷ ቃላቸውን ሰጡ።

ሉዊስ ስትወልድ ደም የፈሰሳት በቀዶ ሕክምና ባለሙያዋ ስህተት መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ እንዳለና ይህ ሰነድ ግን ለቤተሰቡ እንዳልተሰጠ መርማሪው ዶ/ር ቢል ነገሯቸው።

ሉዊስ ጥርጣሬዋ እውነት እንደነበረ በምርመራ ሲረጋገጥ እጅግ ነበር የተበሳጨችው።

“የተፈጠረውን ሊነገሩኝ የሚችሉበት ብዙ ዕድል ነበራቸው። እነሱ ግን ዝምታን መረጡ። ከወለድኩ በኋላ በየሐኪም ቤቱ እየዞርኩ እመረመር ነበር” ብላለች።

የተደረገው ምርመራ ሆስፒታሉ መረጃ እንደደበቀ አጋልጧል። በምላሹ ሆስፒታሉ ይቅርታ ጠይቋል።

ዋና ኃላፊው ትሬሲ “ሉዊስ እና ቤተሰቧን ለተፈጠረው ስህተት እና እንክብካቤ በማጓደላችን ይቅርታ እንጠይቃለን። ሕሙማን ከሚጠብቁት በታች የወረደ አገልግሎት ነበር የተሰጠው” ብለዋል።