በኮንጎ በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ተሳትፏል በሚል የታሰረው አሜሪካዊ ቤተሰቦች ግራ ተጋብተናል አሉ

የ21 ዓመቱ  አሜሪካዊ ታይለር ቶምፕሰን

የፎቶው ባለመብት, Miranda Thompson

ታትሟል

በቅርቡ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተሞክሮ በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት እጁ አለበት በሚል በቁጥጥር ስር የዋለው አሜሪካዊ ቤተሰቦች ግራ ተጋብተናል አሉ።

የ21 ዓመቱ አሜሪካዊ ታይለር ቶምፕሰን ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጋር እንዴት ሊያያዝ እንደቻለ እንደማያውቁም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታይለር የመፈንቅለ መንግሥቱን መርተዋል የተባሉት ልጅ ማርሴል ማላንጋ ጋር ነበር ከአሜሪካ ወደ ወደ ኮንጎ የተጓዘው።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ተሞክሮ ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ጋር ተያይዞ ሶስት አሜሪካውያንን ጨምሮ አምሳ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ታጣቂዎች የኮንጎ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ያለበትን ቤተ መንግሥት ተቆጣጥረው ነበር።

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ማግኘት እንዳልቻሉ የተናገሩት ቤተሰቦች የአሜሪካ የቆንስላ ጽህፈት ቤትም እንዲያየው አልተፈቀደለትም ተብሏል።

ቢቢሲ የኮንጎ ጦር እና የማስታወቂያ ሚኒስቴርን ስለ ጉዳዩ ጠይቋል።

የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የተካሄደው ከዚህ ቀደም ለግዞት በተዳረገው የኮንጎው ፖለቲከኛ ክርስቲያን ማላንጋ እንደሆነ ተነግሯል።

የኮንጎ ጦር በመዲናዋ ኬንሻሳ በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት በሚደረግበት ወቅትም አሻፈረኝ በማለቱ መገደሉ ተገልጿል።

በፕሬዚዳንት ፊሊክስ ታሺኬዲቤተ መንግሥት እና የቀድሞ ኢታማዦር ሹም እና የፕሬዚዳንቱ የቅርብ አጋር በሆኑት ቪታል ካመርሄ ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ስድስት ሰዎች ተገድለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በኬንሻሳ የተቀረጹ ቪዲዮዎች ታይለር በጠመንጃ ሰደፍ በኮንጎ የጸጥታ ኃይሎች ሲመታ አሳይቷል።

የእንጀራ እናቱ ሚራንዳ ቶምፕሰን ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ታይለር መታሰሩን ከተረዱ በኋላ ቤተሰቡ ማመን እንደከበዳቸው ተናግረዋል።

“እዚህ ላይ እንዴት ሊደርስ እንደቻለ ምንም ሃሳብ የለንም። የሆነውን ነገር ስንሰማ በጣም ደነገጥን ” ብለዋል።

ግለሰቧ እንደሚሉት በዩታ ግዛት በግንባታ ድርጅት ይሰራ የነበረው ታይለር ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ጋር እንዴት እንደተያያዘ እርግጠኛ አይደለንም ብለዋል።

ታይለር ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እንዲጓዝ የተጋበዘው በአሜሪካ ተወልዳ ባደገችው የክርስቲያን ማላንጋ ልጅ ማርሴላ እንደሆነ ተናግረዋል። ለመጀመሪያ ጊዜም ነበር ወደ ኮንጎ የሄደው።

የታይለር እና የማርሴላ ጓደኛ የሆነው ዳንኤል ጎንዛሌዝ በበኩሉ ለክርስቲያ ማላንጋ ጥበቃ ለመሆን ከ50-100 ሺህ ዶላር ክፍያ እንደሚፈጸምለት ተነግሮት ወደ ኮንጎ እንዳመራም ነው ለአሶሼትድ ፕሬስ የተናገረው።

የታይለር ቤተሰብ በበኩሉ ይህንን እንደማያውቁ ተናግረዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ቤተሰቡ በኮንጎ የሚገኘው የቆንስላ ጽህፈት ቤት ባለስልጣናት ግለሰቡን ለማየት እንዳልተፈቀደላቸው ተናግረዋል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት አጥቂዎቹ ቀደም ሲል ለግዞት ተዳርጎ ከነበረው ፖለቲከኛ ክርስቲያን ማላንጋ ጋር ግንኙነት ያላቸው የኒው ዛየር ንቅናቄ አባላት እንደሆኑ ነው።

ማላንጋ በሊንጋላ ቋንቋ “እኛ ወታደሮች ደክሞናል፤ ከቪታል ካሜርሄ እና ከፕሬዚዳንት ፌሊክስ ታሺኬዲ ጋር አንድ ላይ መቆም አንችልም” እያሉ የሚናገሩበትን ቪዲዮ ቢቢሲ ተመልክቷል።

ባለፈው ዓመት በታኅሣሥ ወር በተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ታሺኬዲ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠዋል።

ፕሬዚዳንቱ የተመረጡት 78 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ አሸንፈው እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ከምርጫው ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ሁከት ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።

ኮንጎ በወርቅ፣ አልማዝና ማዕድናት የበለጸገች ሃገር ብትሆንም ለዘመናት ይህን ሃብቷ እየተበዘበዘ በውጭ አገራት የሚቸበቸብ ሲሆን ህዝቧም ከድህነት አረንቋ መውጣት አልቻለም።

በግጭቶች በምትናጠው ኮንጎ በርካታ የውጭ አገራት ኩባንያዎች ተሰማርተው ይገኛሉ።