በሩሲያ የአየር ኃይል ሰፈር ላይ ዩክሬን በፈጸመችው ጥቃት የሦስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

ታትሟል

የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች በደቡባዊ ሩሲያ በሚገኝ የአየር ኃይል ሰፈር ላይ በፈጸሙት ጥቃት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ሩሲያ አስታወቀች።

ጥቃቱ የደረሰው በሩሲያ በሚገኘው ኤንግልስ የአየር ኃይል ሰፈር መሆኑንም የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።

የሩሲያ የአየር መከላከያዎች ሰው አልባ አውሮፕላኑን መትተው የጣሉ ሲሆን፣ የወደቀው ቁርጥራጭም ሦስት የቴክኒክ ሠራተኞችን አቁስሏል ተብሏል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ዩክሬን ተመሳሳይ ጥቃት አድርሳለች በሚል ሩሲያ ከሳለች።

ጥቃት ደርሶበታል የተባለው የአየር ኃይል ሰፈር በዩክሬን ላይ የሚሳኤል ጥቃት ለመፈጸም የሚነሱበት እንደሆነም ተነግሯል።

ጣቢያው ከዩክሬን ድንበር በስተሰሜን ምሥራቅ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

የዩክሬን ጦር የቅርብ ጊዜ ጥቃት መፈጸሙን በይፋ ባያምንም የአየር ኃይሉ ቃለ አቀባይ ዩሪ ኢህናት በበኩላቸው ሩሲያ በዩክሬን መሬት ላይ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት ውጤት ነው ብለዋል።

ከጦር ግንባሩ በመቶዎች ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኘው ኤንግልስ የአየር ኃይል ሰፈር ላይ የአሁኑን ጨምሮ ከዚህ ቀደም የደረሱ ጥቃቶች ለሩሲያ ባለሥልጣናት አሳፋሪ ነው ተብሏል።

ሩሲያ ለሦስት አገልግሎት ሰጪዎች ሞት፣ ጉዳቶች እና ሁለት አውሮፕላኖች ቀላል ጉዳት የወደቀውን የሰው አልባ አውሮፕላን ቁርጥራጭ ተጠያቂ አድርጋለች።

ሰኞ ማለዳ ላይ በኤንግልስ የአየር ኃይል ሰፈር አካባቢ ፍንዳታ መድረሱን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ወጥተዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ በዝቅ ባለ ከፍታ ላይ ይበር የነበረውን የሰው አልባ አውሮፕላን መትቶ መጣሉን አስታውቋል።

የሳራቶቭ አስተዳዳሪ ሮማን ቡሳርጊን ለሞቱት ግለሰቦች ቤተሰቦቻቸው እና ዘመዶቻቸው ሐዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በኤንግልስ ከተማ “ለነዋሪዎች ምንም አይነት ስጋት የለም” ሲሉ አረጋግጠዋል።

የዩክሬን አየር ሃይል ቃል አቀባይ የአየር ኃይሉ የሳተላይት ምስሎች በሰኞው ጥቃት የደረሰውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ በቅርቡ እንደሚያሳይ ገልፀው፣ ቀደም ሲል የደረሰው ፍንዳታ በአየር ኃይል ሰፈሩ ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

የኤንግልስ አየር ኃይል ሰፈር በዩክሬን የተለያዩ ኢላማዎች ላይ የሚሳኤል ጥቃቶችን ለመፈጸም ሩሲያ በተደጋጋሚ የምትጠቀምበት ነው።

ሩሲያ ቀደም ሲል ዩከሬን በግዛቴ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች ስትል የከሰሰች ሲሆን፣ ነገር ግን የቅርብ ጊዜው ጥቃቶች ከዩክሬን በመቶ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጠለቅ ብሎ የተፈጸመ ነው።

ከሳምንታት በፊት ዩክሬን የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ በሩሲያ ወታደራዊ ተቋማት ዙሪያ ጥበቃ እንዲጠናከር በከፍተኛ ሁኔራ ቢጠየቅም የቅርብ ጊዜው ጥቃት ይህ እንዳልተከናወነ ይጠቁማል።