ሩሲያ የሠራዊቷን ሞራል ከፍ ለማድረግ ሙዚቀኞችን ወደ ጦር ግምባር ልትልክ ነው

የሙዚቃ ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት እየተዋጉ ያሉትን የሠራዊቷን ሞራል ለማነሳሳት የሙዚቃ ባለሙያዎችን እና አቀንቃኞችን ወደ ጦር ግምባር እንደምትልክ አስታወቀች።

የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የፈጠራ ስራዎችን የሚያቀርብ ብርጌድ መቋቋሙን ያሳወቀ ሲሆን፤ በዚህ ብርጌድ ውስጥ ከሙዚቀኞች በተጨማሪ የሰርከስ ትርኢት የሚያሳዩ ይኖራሉ ተብሏል።

ሩሲያ በጦር ግንባር የጥበብ ስራዎችን ለማቅረብ መዘጋጀቷን የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው የደህንነት መረጃ ጠቅሶት ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ በዩክሬን የጦር ግንባሮችን የሚገኙ ወታደሮች እንደጎበኙ ሞስኮ ገልጻለች።

የመከላከያ ሚኒስቴር በቴሌግራም አማካካኝነት ባሰራጨው መግለጫ ሚኒስትሩ ወታደሮቻቸው በተሰማሩበት ቦታዎች በመዘዋወር የሩሲያን አቅም ተመልክተዋል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ጨምሮም የመከላከያ ሚኒስትሩ “በግንባር የሚገኙ ወታደሮችን ማነጋገራቸውን” ጠቅሷል። ሆኖም ቢቢሲ ጉብኝቱ መቼ እንደተካናወነ እና ሚኒስትሩ ዩክሬን ውስጥ ጉብኝት ስለማድረጋቸው ማረጋገጥ አልቻለም።

ሰርጌይ ሾይጉ ጉብኝት አድርገዋል መባሉን በተመለከተ የዩክሬን ሰራዊት ቃል አቀባይ ሴሪ ቼርቬቲ የሩሲያ መከላከያ ሚንስትር የጦር ግንባሮችን ለመጎበኝት “ይህንን ያህል ልብ አለው ብዬ አላምንም” ሲሉ ለሀገራቸው የቴሌቪዢን ጣቢያዎች ተናግረዋል።

ይህ የተሰማው ዩኬ የሩሲያ የመከላከያ መኮንኖች ሞራል መወደቁን ገልጻ ”በአብዛኛው የሩሲያ ኃይል ተጋላጭነቱ መጨመሩን” ባሳወቀችበት ወቅት ነው።

ዩኬ እንደገለጸችው ቀደም ብሎ የሩሲያ ዜጎች የሙዚቃ መሳሪያዎች ለወታደሮች እንዲለግሱ የተጠየቁበት ይህ የጥበብ ስራ በታሪክ የሚታወቀውን የሙዚቃ እና የመዝነናኛ ፕሮግራምን በጦር ግንባሮች የሰራዊቱን ሞራል ለማነሳሳት ጥቅም ላይ ይውላል።

ሆኖም ይህ በጦር ግንባሮች የሚቀርበው የጥበብ ስራ በርግጥ የሠራዊቱን ሞራል ይገናባል ወይ የሚል ጥያቄ አስከትሏል። ምክንያቱም “በከፍተኛ የጉዳት መጠን፣ በዝቅተኛ የአመራር ብቃት፣ ከክፍያ ጋር በተያያዙ ጥያቄዎች እየተነሱ፣ በመሳሪያ እጥረት እና የጦርነቱን ግብ በተመለከተ ባለው ገልጽነት ጉድለት” ሠራዊቱ እየተፈተነ ስለሆን ነው።

የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት የጥበብ ስራውን የሚያቀርብው ብርጌድ በፕሬዝዳንት ፑቲን የክተት ዘመቻ በፍቃደኝነት ለማገልገል የሚፈልጉ ታዋቂ ሙዚቀኞችን እንደሚያካትት ተመላክቷል።

አዲሱ የጥበብ ብርጌድ “በልዩ ወታደራዊ ዘመቻው እየተሳተፉ ያሉትን ፖለቲካዊ እና ስነ ልቦናዊ ሞራል” ከፍ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል ሲል የመከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።