ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል-ጋዛ፡ የተባበሩት መንግሥታት ራፋህ ላይ የሚፈጸም ጥቃት ወደ “ጭፍጨፋ” ሊያመራ ይችላል አለ
አንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን እስራኤል በራፋህ ላይ ለመፈጸም ያሰበችው ጥቃት ወደ “ጭፍጨፋ” ሊያመራ ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ፤ ጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን “ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እየተሰቃዩ” ነው ብለዋል።
እስራኤል በራፋህ ላይ የምትፈጽመው ወረራ መዘዙ ብዙ ነው የሚሉት ባለሥልጣኑ ነገሮች “ከቁጥጥር ውጭ” ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ራፋህ ተደብቀዋል ያሏቸውን የሐማስ ታጣቂዎች ለመደምሰስ ዝተዋል።
ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ጠንከር ያለ አስተያየት የሰጡት ግሪፊትስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች “ራፋህ ውስጥ ታጉረው፤ ከሞት ጋር ተፋጠዋል” ብለዋል።
አክለውም በከተማዋ ያሉ ሰላማዊ ዜጎች ያላቸው የምግብ ክምችት አነስተኛ፤ የመድኃኒት አቅርቦቱም አሳሳቢ መሆኑን ገልጠዋል።
የተባበሩት መንግሥት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴፋኒ ዱጃሪክ፤ እስራኤል ሰላማዊ ዜጎች ከራፋህ ስለሚወጡበት ሁኔታ ያወጣችው ዕቅድ አልደረሰንም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የተባበሩት መንግሥት ሰዎች ተገደው ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው ሲወጡ ተባባሪ መሆን አይፈልግም” ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ራፋህ በጋዛ ሰርጥ ደቡባዊ ክፍል የምትገኝ ከግብፅ ጋር ድንበር የምትዋሰን አነስተኛ ከተማ ናት።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በከተማዋ 250 ሺህ ሰዎች ይኖሩ ነበር። ነገር ግን እስራኤል በጋዛ ጦርነት ጀምራ ነዋሪዎች ከሰሜናዊው ክፍል እንዲለቁ ካዘዘች በኋላ የራፋህ ነዋሪዎች ቁጥር 1.5 ሚሊዮን ደርሷል።
አብዛኞቹ ፍልስጤማውያን በተወጠረ ጨርቅ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ በሚባል ሁኔታ የሚኖሩ ሲሆን፣ የሚሸሹበት ቦታ የላቸውም።
ከሰሞኑ ራፋህ የእስራኤል ጦር ከባድ ጥቃት እያረፈባት ነው። ሰኞ ዕለት ብቻ 67 ሰዎች ተገድለዋል ይላል በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር።
ግሪፊትስ አክለው በጋዛ ያሉ የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች “ተተኩሶባቸዋል፣ ታግተዋል፣ ጥቃት ደርሶባቸዋል፣ እንዲሁም ተገድለዋል” ብለዋል።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደው የተኩስ አቁም ድርድር ካይሮ ላይ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዩናይት ስቴትስ፣ ከእስራኤል፣ ከግብፅ እና ከኳታር የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማክሰኞ ዕለት ካይሮ ተገናኝተዋል።
እስራኤል ራፋህን ለመውረር ዝግጅት እያደረገች ብትሆንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ይህን እንዳታደርግ በመማፀን ላይ ይገኛል።
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደው ድርድር ውጤቱ ቀና ሆኖ እስራኤል በከተማዋ ላይ ጥቃት እንደማትፈጽም ተስፋ አድርገዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው እስራኤል ሰላማዊ ዜጎችን እንድትጠብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ደግሞ እስራኤል ራፋህን ከመውረሯ በፊት “ቆም ብላ በጥንቃቄ እንድታስብ” መክረዋል።