የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳስ ከእስር መፈታታቸው ተነገረ  

 አቡነ ፍቅረማርያም ሐጐስ

የፎቶው ባለመብት, CATHOLICGHEEZ

የምስሉ መግለጫ, በኤርትራ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሰገነይቲ አገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ፍቅረማርያም ሐጐስ
ታትሟል

በኤርትራ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሰገነይቲ አገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት አቡነ ፍቅረማርያም ሐጐስ ከእስር መፈታታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

ጳጳሱ ከአውሮፓ ጉዟቸው ሲመለሱ በኤርትራ የፀጥታ ኃይሎች ከአሥመራ አየር ማረፊያ ተይዘው የታሰሩት ባለፈው ጥቅምት 05/2015 ዓ.ም. እንደነበረ በኤርትራ እና ከኤርትራ ውጪ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አቡነ ፍቅረማሪያም ሐጎስ ለሁለት ወራት ያህል የት ታስረው እንደቆዩ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ መለቀቃቸውን ግን ጉዳያቸውን በቅርብ ሲከታተሉ የቆዩ ምንጮች አረጋግጠዋል።

ነገር ግን ስለአቡኑ የእስር እና የጤንነት ሁኔታን በተመለከተ እስካሁን የወጣ መረጃ የለም።   

የአቡነ ፍቅረማርያም እስርን ተከትሎ የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክስርቲያን ጳጳሱ ተይዘው ስለሚገኙበት ቦታ እና ሁኔታ የሚመለከታቸውን የኤርትራ ባለሥልጣናት ጥያቄ ባቀረቡበት ጊዜ በቁጥጥራቸው ስር መሆናቸውን ብቻ አሳውቀው ነበር።

የካቶሊክ ሃይማኖት አባት የሆኑትን አቡን እስር በተመለከተ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ከኤርትራ መንግሥት ምንም አይነት መረጃም ሆነ ምክንያት ሳይሰጥ ቆይቶ ነው አሁን የተለቀቁት።

ከአቡነ ፍቅረማርያም ቀደም ብሎ የሰገነይቲ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አገረ ስብከት አስተባባሪ የሆኑት አባ ምህረትአብ እስጢፋኖስ በኤርትራ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው የነበረ ሲሆን፣ እሳቸውም ከአቡኑ ጋር መፈታታቸውን የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋል።

የኤርትራ መንግሥት ጥቂት የማይባሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቀሳውስትን በተለያዩ ጊዜያት በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ ለየትኛውም እስር ግን ይፋዊ ምክንያት ሳይሰጥ ቆይቷል።

በኤርትራ መንግሥት እና በአገሪቱ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት የሻከረ መሆኑ የሚነገር ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ ከእስሩ በተጨማሪ ከሦስት ዓመት በፊት የአገሪቱ መንግሥት ቤተክርስቲያኒቱ የምታስተዳድራቸውን ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ተዘግተዋል።

ከኤርትራ ሕዝብ ውስጥ 4 በመቶ ያህሉ የሮማን ካቶሊክ እምነት ተከታይ ሲሆን፣ በኤርትራ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ከሚፈቀድላቸው አራት ሃይማኖት ተቋማት መካከል አንዱ የካቶሊክ እምነት ነው።

በኤርትራ መንግሥት በእምነት ተቋምነት እውቅና ያላቸው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ የካቶሊክ፣ የሉትራን ወንጌላዊያን እና የሱኒ እስልምና ናቸው።

ከእነዚህ ውጪ ያሉ በተለይም የጴንጤኮስታል እና የኢቫንጀሊካል እምነቶች ተቋማት የውጭ መንግሥታት መጠቀሚያ ናቸው ሲል ይፈርጃቸዋል።

ኤርትራ የእምንት ነጻነትን በመገደብ በኩል በተደጋጋሚ ስትወቀስ የቆየች ሲሆን በዚህም በርካቶች ለእስር መዳረጋቸው ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል።

ከአንድ ዓመት በፊት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ኮሚሽን ኤርትራ በእምንት ነጻነት ላይ በምታደርሰው ጭቆና ምክንያት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በተለየ ሁኔታ እንዲመለከታት ጠይቆ ነበር።