የተመረዘ ገንፎ የበሉ 13 ናሚቢያዊያን የአንድ የቤተሰብ አባላት ሕይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍሪካዊቷ ሃገር በሶስት ቀናት ውስጥ 13 የአንድ ቤተሰብ ሰዎች በምግብ መመዘረዝ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ይህ የሆነው በደቡብ አፍሪካዊቷ ሃገር ናሚቢያ ነው።
የተመረዘ የዳጉሳ ገንፎ የበሉት ናሚያቢያዊያን ከአንድ ቤተሰብ ሲሆኑ 4 ሰዎች ጤናቸው ክፉኛ ተቃውሶ ሆስፒታል ገብተዋል።
የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት አንድ ግቢ ውስጥ የሚኖሩ 22 ሰዎች ናቸው የተመረዘ ገንፎ የበሉት።
ሟቾቹ በሰሜን-ምስራቋ ካቫንጎ አውራጃ በካያቮ መንደር ይኖሩ ነበር።
ከሟቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ ሕፃናት ሲሆኑ ገንፎውን ከመመገባቸው በፊት ረሃብ ላይ እንደነበሩ ተነግሯል።
የሃገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንቢሲ፤ የጤና ሚኒስትሩን ዋቢ አድርጎ ቤተሰቡ የዳጉሳ ገንፎ መብላቱን ዘግቧል።
ቅዳሜ ምሽት የቤተሰቡ አባላት በአካባቢው ወደሚገኝ ሆስፒታል ተልከው ሁለት ከሞቱ በኋላ የተቀሩት ሩንዱ ሰቴት ወደተባ ሆስፒታል ተዘዋውረዋል።
ጣቢያው፤ ቤተሰቡ ከምግብ በኋላ ቤት ውስጥ የተሠራ ቢራ መጠጣታቸውን ጨምሮ ገልጧል።
የናሚቢያ የጤና ሚኒስትር ወደ ሥፍራው የባለሙያዎች ቡድን የላከ ሲሆን ባሙያዎቹ ሃዘን ውስጥ ላለው ቤተሰብ ድጋፍና ምክር ይሰጣሉ ተብሏል።
ተመረዘ ከተባለው ገንፎ የተረፈ ናሙና ወደ ደቡብ አፍሪካ ለምርመራ ተልኳል።
በፈረንጆቹ 2016 የተመረዘ ገንፎ በልተው ቤት ውስጥ በተሠራ ቢራ መሰል መጠጥ ያወራረዱ ሕፃናት መሞታቸው ተዘግቦ ነበር።












