ሩሲያ በጠቀለለቻቸው የዩክሬን ግዛቶች የሚኖሩ ዜጎች እንዲወጡ አሳሰበች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሩሲያ የተሰየሙት የደቡባዊ ዩክሬኗ ኬርሶን መሪ ቭላድሚር ሳልዶ፣ ንጹሃን ዜጎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አሳሰቡ።
ወደከተማው እየተቃረቡ የሚገኙት የዩክሬን ኃይሎች በየቀኑ የሮኬት ጥቃት እያደረሱ በመሆኑ ነው ንጹሃን ዜጎች እንዲወጡ የተነገራቸው።
“ወደ ሩሲያ በመሄድ ራሳችሁን አድኑ” ሲሉ መሪው ለከተማው ነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማራት ኩስንሊንም የኬርሶን መሪ የሰጡትን ማሳሰቢያ አጠናክረዋል።
ዩክሬን በበኩሏ የራሷ ዜጎች የሆኑ ንጹሀን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደማትሰነዝር ገልጻለች።
የዩክሬን ኃይሎች የኬርሶንን ሰሜን ምዕራባዊ አካባቢዎች መልሰው በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋል።
ወደ ኬርሶን መዲናም እየተቃረቡ መጥተዋል።
የግዛቱ አስተዳደር ንጹሃን ዜጎችን ወደሌሎች አካባቢዎች ለማዘዋወረ እንደወሰነ ተገልጿል።
የደቡብ ሩሲያ እና ክሬሚያ አመራር እንዳሉት፣ ለንጹሃን ዜጎች ማረፊያና ሌሎችም አስፈላጊ አገልግሎቶች ይቀርባሉ።
ከኬርሶን የሚወጡ የመጀመሪያው ዙር ሰዎች ዛሬ በሩሲያዋ ሮስቶቭ ይደርሳሉ።
የሮስትቶቭ አገረ ገዢ ቫስሊ ጎሊብቭ ወደ ግዛታቸው የሚገቡ ሰዎችን ለመቀበል ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ዩክሬን ከአሜሪካ የተሰጣትን ሂማርስ ሮኬት ጨምሮ በሌሎችም መሣሪያዎች ታግዛ ነው ኃይሏን ያጠናከረችው።
የዩክሬን ኃይል በሩሲያ የተጠቀለሉ ግዛቶች ላይ አነጣጥሯል።
ከክሬሚያ ውጭ የሚገኙ የዩክሬን ግዛቶች የአየር ጥቃት ሊደርስ ስለሚችል በተጠንቀቅ እንዲጠባበቁ ተነግሯቸው ነበር።
በኪቭ ወታደራዊ ይዞታዎችን ጨምሮ በሌሎችም ቦታዎች ያነጣጠረ የሚሳኤል ጥቃት ተሰንዝሯል።
ሚኢኮሎቭ በተባለው ግዛት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ፣ አንድ ታዳጊ በጥቃት ከፈራረሰ ቤት ሥር ወጥቶ መትረፉ ተገልጿል።
ከኪቭ እና ከሞስኮም የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የ20 ዩክሬናዊ ወታደራዊ አገልግሎት ሰጪዎች እና የ20 ሩስያዊ ወታደሮች ልውውጥ ተደርጓል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቱርኩ አቻቸው ረሲፕ ተይፕ ኤርዶዋን ጋር ሲገናኙ፣ ለአውሮፓ አማራጭ የጋዝ መተላለፊያ በቱርክ እንዲገነባ ተነጋግረዋል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ)፣ ዩክሬን ራሷን ከሩሲያ እና ኢራን ሰው ሠራሽ አውሮፕላኖች እንድትከላከል አስፈላጊውን የጦር መሣሪያ እንደሚለግሱ ገልጸዋል።
በሩሲያ የተሰየሙት የደቡባዊ ዩክሬኗ ኬርሶን መሪ ቭላድሚር ሳልዶ እንዳሉት፣ የዩክሬን ኃይሎች በኬርሶን እና ካክሆቫካ በየቀኑ የሮኬት ድብደባ እያደረጉ ነው።
በድብደባው “ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ” እንደሆነ ገልጸው፣ “ሩሲያ ዜጎቿን ከመጠበቅ ወደኋላ አትልም” ብለዋል።
የዩክሬን ግዛት የሆኑትን ኬርሶን፣ ዛፎሪዛሂያ፣ ዶኔስክ እና ሉሀንስክ ሩሲያ አካል መሆናቸውን ባለፈው ወር ፑቲን ማወጃቸው አይዘነጋም።
ዩክሬን፣ የመንግሥታቱ ድርጅት እንዲሁም የዩክሬን አጋር የሆኑ ምዕራባውያን አገራትም ሩሲያ የዩክሬንን ግዛቶችን መጠቅለሏን አውግዘዋል።












