የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለድሎች ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

ታትሟል

በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን አመርቂ ድል ያስመዘገቡት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን አባላት በአዲስ አበባ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያ ከአዘጋጇ አሜሪካ በመከተል የሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአጠቃላይ 10 ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል።

እነዚህም አራት ወርቅ፣ አራት ብር እና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች ናቸው። በአሜሪካዋ ኦሪጎን ግዛት በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው የሜዳሊያ ብዛት በታሪክ የላቀ ውጤት የተመዘገበበት ነው ተብሏል።

ረቡዕ ምሽት አዲስ አበባ የገቡት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን አባላት ሐሙስ ጠዋት አዲስ አበባ ውስጥ ደማቅ የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ደስተቻቸውን ለመግለጽ ወደ ዋና ዋና መንገዶች የወጡ ሲሆን፣ አትሌቶቹም በከፍት መኪናዎች ላይ ሆነው ታይተዋል።

ቡድኑ ወደ ታላቁ ቤተ-መንግሥት በማቅናት በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እና በሌሎችም ታዋቂ ግለሰቦች አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ታላቅ ድልን ያስመዘገበውን ቡድን አባል የነበረችው እና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆነችው አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለሰጠችው አመራርም አድናቆት ተችሯታል።

ደራርቱ በአትሌቶቹ ውጤት እንደኮራች በመግለጽ፤ በቀጣዩ ውድድር ከባድ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው አውቀው እንዲዘጋጁ አትሌቶቹን አሳስባለች።

ጨምራም ጦርነት ከተካሄደበት የትግራይ ክልል የመጡ አትሌቶች ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት እንዲችሉ የፌደራል መንግሥት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ጠይቃለች።

“ከትግራይ የመጡት አትሌቶች አስካሁን ቤተሰቦቻቸውን የማግኘት ዕድል አላገኙም” ስትል በቤተ-መንግሥት ውስጥ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግራለች።

በውድድሩ ላይ ሦስት ወርቅ ሜዳሊያ ያመጡት ለተሰንበት ግደይ፣ ጎተይቶም ገብረሥላሴ እና ጉዳፍ ፀጋይ ከትግራይ ክልል የመጡ አትሌቶች ናቸው።

በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል የግንኙነት መስመሮች ከተቋረጡ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆነው ይታወቃል።

የገንዘብ ሽልማት

በሥነ ሥርዓቱ ላይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሜዳሊያ ላስገኙ አትሌቶች ከ700ሺህ እስከ 2.5 ሚሊዮን ብር ድረስ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል።

በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ እና በ1 ሺህ 500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያስገኘቸው አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ የ2.5 ሚሊየን ብር ተሸላሚ ሆናለች።

አትሌት ለተሰንበት ግደይ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ በማስገኘቷ 1.5 ሚሊየን ብር እንዲሁም በ5 ሺህ ሜትር ላበረከተችው ውጤታማ የቡድን ሥራ 500 ሺህ ብር በድምሩ የ2 ሚሊየን ብር ተሸላሚ ሆናለች።

በማራቶን ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ላመጡት አትሌት ጎተይቶም ገብረ ሥላሴ እና ታምራት ቶላ እያንዳንዳቸው የ1 ሚሊዮን 750 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።

በወንዶች ማራቶን የብር ሜዳሊያ ያስገኘው ሞስነት ገረመው፣ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ ላስገኘቸው ወርቅውሃ ጌታቸው እንዲሁም በወንዶች 3 ሺህ መሰናክል የብር ሜዳሊያ ላስገኘው ለሜቻ ግርማ ለእያንዳንዳቸው የ1 ሚሊየን ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በ5ሺህ ሜትር እና በ3ሺህ ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኙት አትሌት ዳዊት ስዩም እና መቅደስ አበበ የ700 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷል።