ዩክሬን የአሜሪካን የረዥም ርቀት ሚሳኤል ብትጠቀም ሩሲያ ‘ተጨባጭ’ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩክሬን የአሜሪካን የረዥም ርቀት ሚሳኤል ብትጠቀም፣ ሩሲያ “ተጨባጭና ተገቢ” እርምጃ በመውሰድ ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠነቀቀች።

በሩሲያ ግዛት እንዲህ ያለ ጥቃት ማድረስ የሚያሳየው “አሜሪካና አጋሮቿ በሩሲያ ላይ ቀጥተኛ ጥቃት እንደሰነዘሩ” ነው ብላለች።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን የአሜሪካን የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ዒላማዎችን እንድትመታ መፍቀዳቸው ተገልጿል።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ስለመከተላቸው ግልጽ መረጃ የለም።

ትራምፕ ከሁለት ወራት በኋላ ዋይት ሐውስ በመግባት የአሜሪካንን የመሪነት መንበር ይረከባሉ።

የዩክሬንን ጦርነት በአፋጣኝ እንደሚያቆሙ ደጋግመው ተናግረዋል።

እንዴት ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ትራምፕ በዝርዝር አልተናገሩም። ሚሳኤልን ጥቅም ላይ የማዋል ውሳኔን ሊቀለብሱ ይችላሉ።

ዩክሬን ትጠቀምበታለች የተባለው የረዥም ርቀት ሚሳኤል እስከ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ ይችላል።

የዩናይትድ ኪንግደምና የፈረንሳይ መሣሪያዎችንም ዩክሬን ትጠቀማለች።

የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 1,000 ቀናት ተቆጥረዋል።

ሩሲስያ በዩክሬን መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ያደረሰች ሲሆን፣ አሁን ሩሲያ እና ዩክሬን በጦር ሜዳ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል።

በቅርቡ ሰሜን ኮርያ ከ10,000 በላይ ወታደሮቿ በዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጦር ጋር ተሰልፈው በኩርስክ ግዛት ውስጥ እንዲዋጉ መላኳ ይታወሳል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ስለ ጉዳዩ በቀጥታ አስተያየት ባይሰጡም “ጥቃት የሚሰነዘረው በቃላት አይደለም። ሚሳኤሎቹ መልዕክቱን ያስተላልፋሉ” ብለዋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እስካሁን ምንም አላሉም።

ከዚህ ቀደም ግጭቱ እንዳይባባስ በሚል አሜሪካ በሚሳኤሎቿ ሩሲያ ውስጥ ጥቃት እንዲፈጸም አልፈቀደችም ነበር።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን የምዕራባውያንን የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች እንድትጠቀም መፈቀድ እንደሌለበት አስታውቀዋል።

ፈቃድ ከተሰጠ ግን “ሩሲያ በኔቶ አባላት እንደተቃጣ ቀጥተኛ የጦርነት ተሳትፎ” ትቆጥረዋለች ሲሉ ፑቲን አስጠንቅቀው ነበር።

የፑቲን ቃል አቀባይ አሜሪካ “ጦርነቱ ላይ ጋዝ እያርከፈከፈች ነው” ብለዋል።

የአሜሪካ ምክትል ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጆን ፋይነር፣ “ለሩሲያ ምላሽ እንደምንሰጥ ግልጽ ነበር። የሰሜን ኮርያ ጦር መሠማራትና ሩሲያ የዩክሬንን መሠረተ ልማት መምታቷ ግጭቱን አባብሷል” ብለዋል።

ሩሲያ ባለፉት ቀናት የዩክሬን ኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ጥቃት አድርሳለች። በዚህ ምክንያት መብራት የጠፋ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎችም ተገድለዋል።

ሩሲያ ከሰሞኑ በኦዴሳ ባደረሰችው ጥቃት ተጨማሪ 10 ሰዎች ሲገደሉ፣ 50 ቆስለዋል።

እስካሁን አቋማቸው ምን እንደሆነ ያልተገለጸው ትራምፕ ከሁለት ወራት በኋላ ዋይት ሐውስ ይገባሉ።

አሜሪካ በውጭ አገራት ጦርነት መሳተፍ እንደማትቀጥል መናገራቸው ይታወሳል።

የባይደንን ውሳኔ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አድንቀዋል።

እስካሁን ፈረንሳይም ይሁን ዩናይትድ ኪንግደም ዩክሬን መሣሪያቸውን እንድትጠቀም በመፍቀድ የአሜሪካን መንገድ ስለመከተላቸው በይፋ አልተገለጸም።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ዢፒንግ የዓለም መሪዎች “የዩክሬንን ቀውስ እንዲያረግቡ” ጠይቀዋል።

ቻይና ዋነኛ የሩሲያ አጋር ናት። መሣሪያ ለሩሲያ ሰጥታለች መባሉን ግን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።