ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የለንደን እና የማንቸስተር ደርቢ አሸናፊዎች እነማን ይሆናሉ ?
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከዓለም አቀፍ ጨዋታዎች በኋላ ተመልሷል።
ለንደን፣ ሚድላንድ እና ማንቸስተር የደርቢ ጨዋታዎችን ያስተናግዳሉ።
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን “የሚያሸንፍውን ቡድን ለመምረጥ ቆርጫለሁ” ይላል።
“ከሦስቱ ደርቢዎች አንዱ ለመገመት ቀላል ነው። ሁለቱን ማን እንደሚያሸንፍ መገመት ግን በጣም አስቸጋሪ ነው” ይላል።
ለመሆኑ የሱቶን የፕሪሚየር ሊጉ ግምቶች ምን ይመስላሉ?
ቅዳሜ
አርሴናል ከ ቶተንሃም
አርሴናሎች የውድድር ዓመቱን በድንቅ ሁኔታ ጀምረዋል። ከሰባት ጨዋታ ስድስቱን አሸንፈዋል። በማንቸስተር ዩናይትድም መሸነፍ አልነበረባቸውም።
ቶተንሃምም በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላቸዋል። በአንደዳንድ ጨዋታዎች ዕድለኛ ቢሆኑም ለማሸነፍ ሁሌም ጥሩ መጫወት አይጠበቅባቸውም።
ለሁለቱም ቡድኖች ምክንያት መደርደር ቢቻልም ስሜቴ ወደ አርሰናል ያደላል።
ብዙ ጎል የሚቆጠርበት ጨዋታ ሲሆን አርሴናል በማጥቃት ይጫወታል።
በመልሶ ማጥቃት ለሚጫወተው ቶተንሃም ደግሞ ይህ ምቹ አጨዋወት ነው።
ግምት፡ 3 - 2
በርንማውዝ ከ ብሬንትፎርድ
በምሰጠው ግምት ምክንያት በበርንማውዝ ደጋፊዎች ትችት እየገጠመኝ ነው። ቡድኑ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች አልተሸነፈም።
ከኒውካስትል ጋር ባሳዩት ቁርጠኘነት ብደነቅም በዚህ ጨዋታ ግን አይሳካላቸውም።
ብሬንትፎርዶች ከአርሴናል ጋር በነበረው ጨዋታ ጥሩ ባይሆኑም በዚህ ጨዋታ ወደ አቋማቸው ይመለሳሉ ብዬ አስባለሁ።
በጨዋታው ብዙ ጎሎች የሚቆጠሩ አይመስለኝም።
ግምት፡ 0 - 1
ክሪስታል ፓላስ ከ ቼልሲ
ግርሃም ፖተር ከቼልሲ ጋር በሊጉ በሚያደርጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ምን እንደሚፈጠር መገመት ከባድ ነው።
ቡድኑን በሚፈልጉት መንገድ ለመቅረጽ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል።
እውነታው ግን ዘንድሮ ብዙ የቼልሲ ተጫዋቾች በሚጠበቅባቸው ደረጃ አይደሉም።
ክሪስታል ፓላስ ነገሮችን ጠንካራ ቢያደርገውም ሰማያዊዎቹ የበላይ ሆነው ያጠናቅቃሉ።
ግምት፡ 1 - 2
ፉልሃም ከ ኒውካስል
ኒውካስል ዘንድሮ አንድ ጨዋታ ብቻ ቢያሸንፍም አጨዋወቱ ተመችቶኛል።
ቡድኑ አጥቂዎቹን ስለማያገኝ የፊት መስመር ከፍተት አለበት።
ስለዚህ ይህ ጨዋታ አቻ የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።
ፉልሃም የውድድር ዓመቱን የጀመረበት መንገድ አስደንቆኛል።
ግምት፡ 1 - 1
ሊቨርፑል ከ ብራይተን
ብራይተን በፖተር አሰልጣኝነት በሊቨርፑል ሜዳ ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል። በአሰልጣኝ ሮቤርቶ ዲ ዜርቢ ስር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የምናያቸው ይሆናል።
ማጥቃትን የሚመርጡ አሰልጣኝ ሲሆኑ አንፊልድ ላይ ይሞክሩት ይሆን የሚለውን እናያለን።
ጥሩ አጀማመር ላልነበረው ሊቨርፑል ሊጉ በመሐል መቋረጡ እንደ አዲስ ለመጀመር ዕድል ሊፈጥርለት ይችላል።
ቀጣዩ ወር ወር ብዙ ጨዋታ የሚያደርጉበት ስለሆነ ወደ አቋማቸው በፍጥነት መመለስ ይጠበቅባቸዋል።
ግምት፡ 3 - 1
ሳውዝሃምፕተን ከ ኤቨርተን
ስለ ሳውዝሃምፕተን አንዳንዴ ድንቅ ቡድን ይሆናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ይጠፋል።
ኤቨርተን እየተሻሻለ ነው።
በዘንድሮው ዓመት ብዙ አቻ እየወጣ የሚመስለው ኤቨርተን በዚህ ጨዋታም ነጥብ ይጋራል ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 1 - 1
ዌስት ሃም ከ ዎልቭስ
ዲዬጎ ኮስታ በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ የዎልቭስ ጨዋታዎችን ሊያደርግ ይችላል።
አጥቂው በቀድሞ ድንቅ አቋሙ ላይ አይደለም።
ዎልቭስ ድንቅ ቡድን ቢሆንም በማጥቃት መስመር ላይ ክፍተት አለበት። ኮስታ ይህንን ችግር የሚሸፍን አይመስለኝም።
ዌስት ሃምም ድንቅ ጉዞ ባያደርግም በዚህ ጨዋታ ነገሮች ይቀየራሉ ብዬ እገምታለሁ።
ግምት፡ 1 - 0
እሑድ
ማንቸስተር ሲቲ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ማንቸስተር ዩናይትድ በኤሪክ ቴን ሃግ ስር መሻሻል እያሳየ ቢሆንም በሊጉ ምርጥ ከሆነው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ነው የሚገጥመው።
አርሴናል ከዩናይትድ ጋር በነበረው ጨዋታ ዕድሎችን መፍጠር ቢችልም አልተጠቀመባቸውም።
ሲቲዎች ባስለመዱት መንገድ ስለሚጫወቱ ዕድሎቹን ይጠቀማሉ።
ዩናይትድ በመልሶ ማጥቃት ችግር ለመፍጠር ቢሞክርም በጨዋታው ይሸነፋሉ።
ግምት፡ 4 - 1
ሊድስ ከ አስቶን ቪላ
የሊድሱ አሰልጣኝ ጄሴ ማርሽ ከብሬንትፎርድ ጋር በነበረው ጨዋታ ቀይ ካርድ ስለተመዘዘባቸው ይህንን ጨዋታ አይመሩም።
ቡድናቸው በተለመደው ፍጥነት የሚጫወት ሲሆን በኤላንድ ሮድ መጫወታቸው ደግሞ ይበልጥ ያነሳሳቸዋል።
በሜዳቸው የሚሳካለቸው ይመስላል።
ቪላዎች ከሜዳቸው ውጭ ጥሩ ባይሆኑም ሳውዝሃምፕተንን ማሸነፋቸው ድንቅ ውጤት ሆኖላቸዋል።
ከሜዳቸው ውጭ ያደረጉትን ሦስት ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፈዋል።
ግምት፡ 2 - 1
ሰኞ
ሌስተር ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ሁለቱም የሊጉ ግርጌ ላይ ያሉ ቡድኖች በመሆናቸው ምንም ነገር ሊፈጠር ይችላል።
ሌስተር ከቶተንሃም ጋር ጥሩ ለመጫወት ቢሞክርም ሲከላከል ደካማ ነበር።
ጫና ውስጥ የሚገኙት አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ይህንን ጨዋታ ቢሸነፉም ይባረራሉ ብዬ አላስብም።
ሊጉ ለዓለም ዋንጫ ከመቋረጡ በፊት ቡድኑ ግን መሻሻል ይጠበቅበታል።
ፎረስትም እየተሸነፈ ቢሆንም ቡድኑ ውስጥ ካለው ለውጥ አንጻር ለአሰልጣኝ ስቲቭ ኩፐር አዝንለታለሁ።
ቡድኑ እስኪዋሃድ ጊዜ የሚፈልግ ሲሆን ይህ ደግሞ ከባድ ነው።
ግምት፡ 2 - 1