እስራኤል ለጋዛ ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት እንዲሰጥ ውጊያ ለማቆም ተስማማች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

እስራኤል በጋዛ ለሚገኙ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት እንዲሰጥ “ለሰብአዊ እርዳታ” በሚል ውጊያዋን ለመግታት እንደተስማማች የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።

ይህ የክትባት ዘመቻ በመጪው ዕሁድ ነሐሴ 26/2016 ዓ.ም. የሚጀምር እንደሆነና በጋዛ ሰርጥ ለሚገኙ ወደ 640 ሺህ የሚጠጉ ህጻናትን እንደሚሰጥ የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ሪክ ፒፒርኮን ተናግረዋል።

ክትባቱ በማዕከላዊ፣ ደቡባዊ እና ምስራቃዊ የጋዛ ክፍሎች በሦስት የተለያዩ ዙሮች ይሰጣል። በተከታታይ ለሚደረገው የክትባት ዘመቻ በሚል ለተከታታይ 3 ቀናት በየዕለቱ ለ9 ሰዓታት ውጊያ ይቆማል።

እስራኤል ለዚህ የክትባት ዘመቻ ከመስማማቷ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ከ25 ዓመታት በኋላ በጋዛ የመጀመሪያው የፖሊዮ ተጎጂ መገኘቱ ተሰምቷል። የተመድ ባለስልጣናት አንድ የ10 ወር ጨቅላ በፖሊዮ ምከንያት ከፊል አካሉ መታዘዝ እንዳቆመ ተናግሯል።

በጠብታ መልክ በአፍ የሚሰጠው ታይፕ 2 የተባለው የፖሊዮ ክትባት ወደ ጋዛ የተላከ ሲሆን ተጨማሪ 400 ሺህ ጠብታ ክትባት በቅርቡ እንደሚደርስ ይጠበቃል።

የክትባት ዘመቻውን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር የሚያስተባብረው ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩኒሴፍ እና ሌላ የመንግስታቱ ድርጅት ተቋም ይሳተፍበታል።

ከ2 ሺህ የሚልቁ የጤና ባለሙያዎች እና የማህበረሰብ አስተባባሪዎች ለዚህ የክትባት ዘመቻ ስልጠና ወስደዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ ሰርጥ የፖሊዮ ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል 90 በመቶ የክትባት ሽፋን ለመስጠት እንዳቀደ ገልጿል።

አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ክትባቱን ለማዳረስ ለተጨማሪ ለአራተኛ ቀን ተኩስ የማቆም ስምምነት ተደርሷል።

የፖሊዮ ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የመስፋፋት አቅም ያለው ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በቆሸሸ ፍሳሽ እና በተበከለ ውሃ አማካኝነት ይሰራጫል።

ቫይረሱ የፊት ቅርጽ መዛባትን እና የሰውነት አለመታዘዝን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን እጅግ ከከፋም ለሞት ሊዳርግ ይችላል።

የዓለም ጤና ድርጅት የመጨረሻው ጦርነት ከመቀስቀሱ አስቀድሞ በጋዛ እና በእስራኤል ቁጥጥር ባለው ዌስት ባንክ የነበረው የበሽታ መከላከል ምጣኔ የተሻለ የሚባል እንደነበር ገልጿል።

በአውሮፓውያኑ 2022 የነበረው የፖሊዮ ክትባት ሽፋን 99 በመቶ የነበረ ቢሆንም ባለፈው ዓመት ወደ 89 በመቶ አሽቆልቁሏል።

ባለፈው ወር የእስራኤል ጦር በሽታውን ለመከላከል ወታደሮቹን መከተብ እንደጀመረ ገልጾ ነበር።

የሐማስ ባለስልጣናት ይህ ክትባት እንዲሳካ እና ከ6 መቶ ሺህ በላይ ህጻናትን ለመታደግ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነን ሲሉ ይናገራሉ።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚደረገው ጦርነቱን ውጊያውን መግታት እንጂ “ተኩስን ማቆም” አይደለም ብለዋል።