ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሉትን የነዳጅ ዋጋ ገደብ ደካማ ነው አሉ

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE

ታትሟል

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ምዕራባውያን በሩሲያ ወጪ ንግድ ላይ የጣሉትን የነዳጅ ዋጋ ገደብ “ደካማ” ነው ሲሉ ተቹ።

አርብ ዕለት የጸደቀው የዋጋ ገደብ የሩሲያን ድፍድፍ ነዳጅ የሚገዙ አገራት በበርሜል ከ60 ዶላር በላይ እንዳይከፍሉ ለማድረግ ያለመ ነው።

ሩሲያ በነዳጅ ምርቶች ወጪ ንግድ ላይ የተጣለውን የዋጋ ገደብ እንደማትቀበል አሳውቃለች።

በመጪው ሰኞ ተግባራዊ የሚሆነው የዋጋ ጣሪያ ምዕራባውያን ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከፈጸመችው ወረራ ጋር ተያይዞ እያደረጉት ያለው ጫና አካል ነው።

ነገር ግን ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ የዋጋ ጣሪያውን የምዕራባውያንን ደካማ አቋም ያንጸባረቀ ነው ሲሉ ተችተዋል።

የሩሲያ ምጣኔ ኃብትም ላይ የረባ የሚባል ጫናም አያሳርፍም፤ ጉዳትም አያደርስም ብለዋል።

“ሩሲያ ሆን ብላ የዓለምን የገበያ ስርዓት በማወክ በሁሉም የአለም ሃገራት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሳለች” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

“በአሁኑ ወቅት ጠንከርና ጠበቅ ያሉ እርምጃዎች ጥቅም ላይ የሚውሉበት ነው” ሲሉም አክለዋል።

የዋጋ ጣሪያው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታካሂደውን ጦርነት የገንዘብ አቅም ለማዳከም አልሟል።

ይህንንም ፕሮፖዛል ያቀረቡት በኢንዱስትሪ የበለጸጉት የቡድን ሰባት አገራት (አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን እና የአውሮፓ ህብረት) ናቸው።

የቡድን ሰባት አገራት ባወጡት የጋራ መግለጫ የአውሮፓ ህብረት እና አውስትራሊያ እርምጃው የተወሰደው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከምታካሂደው ወራራ ትርፍ እንዳታገኝ ለማድረግ ነው ማለታቸው ሰፍሯል።

ቅዳሜ ዕለት የክሬምሊን ቃለ አባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሩሲያ ለዚህ እርምጃ ዝግጁ መሆናቸውን ቢያሳውቁም አገራቸው የዋጋ ጣሪያውን አትቀበለውም ብለዋል ።

የሩሲያ ነዳጅ ላይ የሚደረገው የምዕራባውያኑ ጫና ሞስኮ ላይ ተጽእኖ ቢኖረውም፣ በአሁኑ ወቅት የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ቀዳሚ ገዢዎች በሆኑት እንደ ሕንድ እና ቻይና ባሉ ገበያዎች ይካካሳል ተብሏል። 

የዋጋ ጣሪያው ስምምነት ተግባራዊ የሚሆነው የአውሮፓ ህብረት በባህር በሚገባው የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ላይ የተጣለው እገዳ ተፈጻሚ በሚሆንበት በተመሳሳይ ዕለት ነው።

አዲሱ የዋጋ ጣሪያ እርምጃ በዓለም ዙሪያ ያለውን የነዳጅ ወጪ ንግድ ላይ ተፅእኖ የሚያሳድር ነው።

በቡድን 7 አማካኝነት የቀረበውን የነዳጅ ዋጋ ጣሪያ ውሳኔን የፈረሙ አገራት በባሕር በኩል የሚያስገቡትን ነዳጅ መግዛት የሚችሉት በስምምነቱ በተቀመጠው ወይም ከዚያ በታች በሆነ ዋጋ ነው። 

የዩክሬን ምዕራባውያን አጋሮች በዋጋ ጣሪያው ስምምነት ላይ ያልፈረሙ አገራት የሩሲያን ነዳጅ ለሚያደርሱላቸው ተሽከርካሪዎች የሚሰጠውን መድህን እንደሚከለክሉ ገልጸዋል።

ይህም ሩሲያ ነዳጇን ከተቀመጠው ዋጋ በላይ እንዳትሸጥ የሚያደርግ ነው።