ፖሊስ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ዋና ሥራ አስፈጻሚ ግድያ ላይ ምርመራ መክፈቱን አስታወቀ

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለባቸው አሞኜ

የፎቶው ባለመብት, Kirkos Woreda 8 communication

የምስሉ መግለጫ, የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለባቸው አሞኜ
ታትሟል

በቢሮ ውስጥ በሥራ ላይ እያሉ መፈደላቸው የተገለጸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለባቸው አሞኜ ግድያ ላይ ምርመራ መክፈቱን ፖሊስ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ግድያውን የፈጸመው የማኅበረሰብ አገልግሎት ፖሊስ አባል የሆነው ተጠርጣሪ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት ነው።

ዛሬ አርብ ግንቦት 04/2015 ዓ.ም. ለተፈጸመው ግድያ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ፖሊስ በምርመራ እያጣራ እንደሆነ የጠቀሱት ኮማንደሩ ምርመራውን ከተጠናቀቀ በኋላም ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል።

ግድያውን በተመለከተ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተለያዩ መላምቶች እየተነገሩ ሲሆን፣ ከነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች ሕብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ ኮማንደሩ አሳሳስበዋል።

“ከዚህ ግድያ ጋር በተገናኘ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለራሳቸው አጀንዳ በሚያመች መልኩ የተለያዩ ሃሳቦችን የሚገልጹ ግለሰቦችን እያየን ነው” ያሉት ኮማንደሩ ማኅበረሰቡ ከፖሊስ መረጃ እንዲያገኝ ጠይቀዋል።

የፖለቲካ ግድያ ነው የሚያስብለው ጉዳይ አለ ወይ? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮማንደሩ በሰጡት መልስ “አንዳችም ነገር የለም” በማለት ምክንያቱ በሚካሄደው ምርመራ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል።

“ሆኖም እስካሁን ፖሊስ ባረጋገጠው መሠረት ግድያው ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንድምታ የለውም” ሲሉ አክለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚው የሆኑት አቶ አለባቸው አሞኜ ዛሬ ግንቦት 4/2015 ዓ.ም ጥዋት 4 ሰዓት ላይ አገልግሎት ሊያገኝ በመጣ የአካባቢው የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አባል ነው በቢሯቸው ውስጥ በሽጉጥ የተገደሉት።

ግድያውን የፈጸመው ግለሰብ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የካዛንቺስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት የቀጠና ኦፊሰር መሆኑንም ኮማንደር ማርቆስ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መረጃ ግለሰቡ የግል ጉዳዩ እንዲፈጸምለት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 8 አስተዳደር ጽህፈት ቤት አመልክቶ እንደነበር ገልጿል።

ፖሊስ ምን እንደሆነ ያልጠቀሰው ይህ የግል ጉዳይን በተመለከተ ወረዳው ተመልክቶ ምላሽ እንደሚሰጠው ተነግሮታል።

ነገር ግን ጉዳዬ “ምላሽ እንዳያገኝ የከለከልከው አንተ ነህ በሚል ምክንያት” የወረዳውን ሥራ አስፈጻሚ በታጠቀው ሽጉጥ መግደሉም ሰፍሯል።

“አቶ አለባቸው በሥራ ቁርጠኝነት የሚታወቁ፣ በበርካታ መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ተግባራት አርዓያነት ያለው ሥራ የሰሩ እና ያስተባበሩ አመራራችን ነበሩ” ሲልም የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ኮሚዩኒኬሽን ሐዘኑን ገልጿል።