በካናዳ አምስት ሚሊዮን ንቦች ከመኪና ወደቁ

ታትሟል

በካናዳ በጭነት መኪና ሲጓዙ የነበሩ አምስት ሚሊዮን ንቦች ከመኪናው መውደቃቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ንብ አናቢዎች ንቦቹን በመሰብሰብ እርዳታ ሰጥተዋል።

ማይክል ባርበር የተባለ ንብ አናቢ ከፖሊሶች ተደውሎለት ነበር ቦታው ላይ የደረሰው።

አምስት ሚሊዮኑ ንቦች ቀፎ ውስጥ ሆነው እየተጓዙ ሳለ ቀፎው የታሰረበት ገመድ በመላላቱ ነበር ከጭነት መኪናው ተንከባለው የወደቁት።

ንብ አናቢው እንደሚለው አካባቢው በንቦች ለመወረር ጊዜ አልወሰደበትም።

“በጣም ብዙ ንቦች ነበሩ። ከቀፎው ስለወጡ ግራ ተጋብተውና ተቆጥተውም ነበር” ብሏል።

በአካባቢው የነበሩ አሽከርካሪዎች መስኮታቸውን እንዲዘጉ እግረኞችም ከአካባቢው ዘወር እንዲሉ ተነግሯቸዋል።

በካናዳዋ ኦንታሪዮ በምትገኘው ቡርሊንግተን የተፈጠረው የንቦች ግርታ በ11 ዓመታት የንብ አናቢነት ሕይወቱ አይቶት የማያውቅ መሆኑን ማይክል ገልጿል።

“ከዚህ በኋላ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዲገጥመኝ አልመኝም” ብሏል ለቢቢሲ።

‘ትራይ ሲቲ’ የተባለ የንብ ማቆያ ያለው ማይክል ከፖሊስ ተደውሎለት ነበር ስለክስተቱ የተነገረው።

ለሌሎች ንብ አናቢዎች ደውሎም በቦታው ተገኝተዋል።

ፖሊስ ለንብ አናቢዎች ከመደወሉም በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያም የእርዳታ ጥሪ አድርጓል።

ማይክል እንደሚለው ንቦቹ በ400 ሜትር ርቀት ተበትነው ነበር። በአካባቢው ባሉ መኪኖችና ሌሎችም መጠለል የቻሉባቸው ቦታዎች አርፈዋል።

“በሺዎች የሚቆጠሩ ንቦች መኪናዬ ላይ ብቻ አርፈው ነበር” ይላል ንብ አናቢው።

ከሰዓታት በኋላ ንቦቹን በቀፎ ማስገባት ተችሏል። ቀፎ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንቦች ሞተዋል።

በሂደቱ በንብ የተነደፉ ንብ አናቢዎችም ነበሩ። የጭነት መኪናው አሽከርካሪ ከ100 ጊዜ በላይ ተነድፏል።

በቦታው ሐኪሞች ስለነበሩ እርዳታ ሰጥተዋል።

ንብ አናቢዎች ተረባርበው ንቦቹን ቀፎ ውስጥ በማስገባታቸው ሰዎችን ከአደጋ ማዳን እንደቻሉም ተገልጿል።