ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲስ በተጀመረው የጋዛ ተኩስ አቁም ድርድር ሃማስ ተጨማሪ ታጋቾችን ለመልቀቅ ሃሳብ አቀረበ
ሃማስ ቅዳሜ ዕለት አዲስ የተኩስ አቁም ድርድር ከተካሄደ በኋላ ተጨማሪ ታጋቾችን ለመልቀቅ ሃሳብ አቀረበ።
ንግግሩ የተጀመረው የእስራኤል መከላከያ በጋዛ ሰርጥ አዲስ የተጠናከረ ወታደራዊ ጥቃት በጀመረ በሰዓታት ውስጥ ነው።
ሃማስ ለ60 ቀናት የተኩስ አቁም ዘጠኝ ታጋቾችን ለመልቀቅ ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን እስራኤል በበኩሏ እስረኞችን እንደምትለቅ የፍልስጤም ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለሥልጣናቱ አዲሱ የታቀደው ስምምነት መሰረት በቀን 400 የእርዳታ መኪኖች እንዲገቡ እና ሕሙማን ለሕክምና ከጋዛ መውጣት ያስችላል ብለዋል።
እስራኤል በበኩሏ ቀሪዎቹ ታጋቾች በሕይወት መኖራቸውን እና ስለ ሁሉም ዝርዝር መረጃ ማግኘት ትፈልጋለች።
አዲሱ የተኩስ አቁም ድርድር በኳታር እና በአሜሪካ አደራዳሪነት በዶሃ እየተካሄደ ሲሆን የተጀመረው ቅዳሜ ከሰዓት መሆኑ ታውቋል።
እስራኤል እስካሁን ድረስ ሃማስ ባቀረበው ሃሳብ ላይ በይፋ መልስ አልሰጠችም።
ነገር ግን ከንግግሩ በፊት ከጋዛ ወታደሮቿን እንደማታስወጣ እና ጦርነቱን ለማቆም ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ እንደማትደርስ ማሳወቋ ተገልጿል።
ቢቢሲ መረዳት እንደቻለው የቀረበው ምክረ ሃሳብ እነዚሀን አያካትትም።
የእስራኤል መከላከያ ቅዳሜ ማለዳ "ዘመቻ የጌዲዮን ሰረገላ" ሲል የሰየመው እና የከፈተው አዲስ ጥቃት በጋዛ ለወራት ከታዩት ወታደራዊ እርምጃዎች ሁሉ የከፋው ነው ተብሏል።
ከሐሙስ ጀምሮ በሰሜናዊ እና ደቡባዊ የጋዛ ሰርጥ በሆስፒታል፣ በመጠለያ ጣብያዎች ጨምሮ ቢያንስ 300 ሰዎች በእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ መሞታቸውን የሕይወት አድን ሠራተኞች ተናግረዋል።
ለሁለት ወር የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት መፍረሱን ተከትሎ እስራኤል ዳግም ወታደራዊ ጥቃቷን እአአ መጋቢት 18 ከጀመረች በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የእርዳታ ድርጅቶች በጋዛ ያለው አሰቃቂ የሰብዓዊ እርዳታ ሁኔታ ተባብሷል ሲሉ የተናገሩ ሲሆን እስራኤል ማንኛውንም ወደ ጋዛ የሚገባ የምግብ፣ የመድሃኒት፣ እንዲሁም ሌሎች የእርዳታ ቁሳቁሶች ለ10 ሳምንታት አግዳ ቆይታለች።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በወሩ መጀመርያ ላይ ሃማስን "ለማውደም" እንዲቻል ጋዛን ለመውረር እና በቁጥጥር ስር አውሎ ማቆየት የሚያስችል ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚያካሄዱ ዝተው ነበር።
በጋዛ የምትገኘው ጋህዳ አል ቁራድ የተሰኘች ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ኒውስ አወር ፕሮግራም እንደተናገረችው ከሆነ " በምሥራቅ እና ሰሜን ጋዛ በርካታ የአየር ጥቃቶች፣ የሚሳዔል ድብደባዎች፣ ተኩሶች እና ፍንዳታዎች" እየተካሄዱ ነው።
"አስፈሪ እና አሰቃቂ ነው" ስትል አክለላች።
በጋዛ ባለው የምግብ እጥረት እና የምግብ ዋጋ መናር የተነሳ ቤተሰቧ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ መመገብ አንሚችል የገለፀችው ጋዜጠኛዋ፣ እስራኤል "ምግብን እንደ መሣርያ እየተጠቀመችበት ነው" ስትል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ከሳምንት በፊት የተናገሩትን ደግማለች።
የእርዳታ ድርጅቶች በጋዛ ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ሕዘብ ለረሃብ መጋለጡን ያስጠነቀቁ ሲሆን የእስራኤል እርዳታ ማገድን ተከትሎ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕጻናትን የሚያሳዩ ምስሎች ከአካባቢው መውጣት ጀምረዋል።
አርብ ዕለት የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ "በርካታ ሰዎች ተርበዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
የእስራኤል መንግሥት በተደጋጋሚ በጋዛ የምግብ እጥረት የለም ሲል ያስተባብላል።
በካህን ዩኒስ በናስር ሆስፒታል የምትሰራው ብታንያዊቷ ዶክተር ቪክቶሪያ ሮዝ ለቢቢሲ ሬዲዮ 4 ቱዴይ ፕሮግራም እንደተናገረችው፣ባልደረቦቿ "ተዳክመዋል" የሆስፒታሉ "ሠራተኞችም ቢሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ክብደት ቀንሰዋል" ብላለች።
"ሕጻናቱ በጣም ቀጫጫ ናቸው" ስትል አክላ "ጥርሳቸው የረገፈ በርካታ ታዳጊዎች እያገኘን ነው" ብላለች።
"ብዙዎቹ የቃጠሎ ጉዳት አጋጥሟቸው ይመጣሉ። ካሉበት ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት የተነሳ ለኢንፌክሽን ተጋላጭ ናቸው ለመዳን ያላቸው አቅምም በጣም አነስተኛ ነው" ብላለች።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሚያዝያ 27 2017 ዓ.ም. በጋዛ "ከባድ የሆነ ማጥቃት" ለመክፈት እና በወረራ ግዛት ለመያዝ እየተዘጋጁ መሆኑን አስታወቀው፣ ይህ ግን ትራምፕ በባህረ ሰላጤው የሚያደርጉትን ጉብኝት እስኪጨርሱ ድረስ እንደማይሆን ተናግረው ነበር፥
ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ ያደረጉትን ጉብኝት አርብ ዕለት አጠናቅቀዋል።
አርብ ዕለት በጋዛ ሰሜናዊ እና ማዕከላዊ ክፍል የሚኖሩ ፍልስጤማውያን አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ የተነገራቸው ሲሆን የእርዳታ ሠራተኞች፣ ነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ በመደረጋቸው እና ቤት አልባ በመሆናቸው ፈጽሞ ተግባራዊ ለመሆን የማይችል ትዕዛዝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ቅዳሜ ዕለት "ሃማስ ዳግመኛ ስጋት መሆኑ እስኪያበቃ እና ታጋቾች በሙሉ ወደ ቤተሰባቸው እስኪቀላቀሉ ድረስ" ጥቃቱን እንደማያቋርጥ ተናግሯል።
መከላከያው አክሎም በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ "150 የሽብር ዒላማዎችን በመላው የጋዛ ሰርጥ" መምታቱን አስታውቋል።
በሺህዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ወታደሮች፣ የተጠባባቂ ኃእሎችን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ጋዛ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የእስራኤል ታንኮች በድንበሩ አቅራብያ መታየታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
እስራኤል አጠናክራ የቀጠለችው ወታደራዊ ጥቃት በአውሮፓ ኅብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቃውሞ ገጥሞታል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 7/2023 ቡድኑ እስራኤል ላይ ጥቃት አድርሶ 1,200 ሰዎች መገደላቸውን እና 251 ሰዎች መታገታቸውን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ሃማስን ለማጥፋት ወታደራዊ ዘመቻ ጀምሯል።
እስካሁን ድረስ በጋዛ ቢያንስ 53,000 ሰዎች በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።