የቤት ውስጥ ጥቃት “አድራሾች” የጦር መሳሪያ እንዳይኖራቸው የአሜሪካው ፍርድ ቤት ወሰነ

ታትሟል

በቤት ውስጥ ጥቃት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች የጦር መሳሪያ ባለቤት ሊሆኑ አይችልም ሲል የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ።

እነዚህ ተጠርጣሪዎች የቤት ውስጥ ጥቃት በፈጸሙባቸው ግለሰቦች አካባቢ ድርሽ እንዳይሉም በፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ የተጣለባቸው ናቸው።

ውሳኔው በቤት ውስጥ ጥቃት ተጠርጥረው የእግድ ትዕዛዝ በፍርድ ቤት የተጣለባቸው ግለሰቦች የጦር መሳሪያ ለ30 ዓመት ያህል ሊኖራቸው እንደማይችል አስቀምጧል።

ታችኛው ፍርድ ቤት ይህንን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ “ከሃገሪቱ ታሪካዊ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ባህል ጋር የማይጣጣም” በማለት ውድቅ አድርጎታል።

አርብ ዕለት ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የጦር መሳሪያዎችን በተመለከተ ባልተለመደ መልኩ እገዳ ማስተላለፉ እንደ ድል ታይቷል።

ዋና ዳኛ ጆን ሮበርትስ ከአንዱ ዳኛ በስተቀር ሁሉም በስምምነት ያሳለፉትን ውሳኔ አሰምተዋል።

የቤት ውስጥ ጥቃት አድራሾችን ትጥቅ የማስፈታት ፖሊሲ “ጤነኛ አዕምሮ ሊያደርገው የሚገባ ነው” ሲሉም ጽፈዋል።

ውሳኔውን በብቸኝነት የተቃወሙት ዳኛ ክላረንስ ቶማስ በወግ አጥባቂነታቸው ይታወቃሉ።

የዛሬው ውሳኔ “‘ሰከንድ አሜንድመንት’ የተሰኘውን ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን የነጻነት መብት አደጋ ላይ የጣለ ነው” ብለዋል።

አርብ ዕለት በተላለፈው ውሳኔ መሃልም በሴት ጓደኛው ጥቃት በማድረስ እንዲሁም በሕዝብ ቦታዎች ላይ ተኩስ በመክፈት የተፈረደበት ዛኪ ራሂሚ የተባለው የቴክሳስ ነዋሪ ጉዳይ ተነስቷል።

ግለሰቡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሴት ጓደኛውን መኪና ውስጥ ጎትቶ በማስገባት ጭንቅላቷን ከመኪናው ጋር እንዳጋጫትና እንዲሁም ጥቃቱን በታዘበ ግለሰብም ላይ ተኩስ ከፍቶ ነበር።

የሴት ጓደኛው በፍርድ ቤት ውሳኔ የእግድ ትዕዛዝ እንዲጣልበትም ማድረግ ችላ ነበር። በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ የጦር መሳሪያ ፍቃዱ እንዲታገድ እና ምንም አይነት መሳሪያ እንዳይዝ በግለሰቡ ላይ እግድ ቢጥልበትም ይህንን ተላልፎ በሕዝባዊ ቦታ በአምስት ሰዎች ላይ ተኩስ መክፈቱ ተሰምቷል።

ግለሰቡ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመጣስ ጥፋተኝነቱን ያመነ ሲሆን የስድስት ዓመት እስርም ተፈርዶበታል።