የ101 ዓመቱ የናዚ ጥበቃ፣ ሰዎች እንዲገደሉ በመተባበር አምስት ዓመት ተፈረደባቸው

ታትሟል

የቀድሞው የናዚ የማጎሪያ ካምፕ ጠባቂ የነበሩት የ101 ዓመቱ ግለሰብ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ ድጋፍ በማድረጋቸው የተነሳ የአምስት ዓመት እስራት ተፈረደባቸው።

ጆሴፍ ኤስ የተባሉት ግለሰብ በርሊን አቅራቢያ የሚገኘው ሳችሴንሃውሰን የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ጠባቂ ነበሩ።

በጀርመን ፍርድ ቤት በመቅረብ በዕድሜ ትልቁ የናዚ አባል ሲሆኑ፣ ኤስኤስ የተባለው የናዚ ጥበቃ ቡድን ባልደረባ መሆናቸውን ክደዋል።

ነገር ግን ግለሰቡ በቀረበባቸው ክስ 3,518 ሰዎች እንዲገደሉ በመተባበር ወንጀለኛ ሆነው ተገኝተዋል።

የሶቪየት ኅብረት የጦር ምርኮኞችን ጨምሮ ሌሎችንም ሰዎች 'ዛይክሎን ቢ' በተባለው መርዛማ ጋዝ በመግደል ተባብረዋልም ተብሏል።

የ101 ዓመቱ ጆሴፍ ፍርዱን ተቃውመው ይግባኝ እንደሚሉ ተገልጿል።

ከዚህ በኋላ የጀርመን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የይግባኝ ጥያቄያቸውን እስከሚያይ ድረስ ወራት እንደሚወስድም ተነግሯል።

እስከዚያ ድረስም የተፈረደባቸውን ዓመታት በእስር ላያሳልፉ ይችላሉ።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሳችሴንሃውሰን የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ተገድለዋል።

ከእነዚህ መካከል በረሃብ፣ በግዳጅ የጉልበት ሥራ፣ በኤስኤስ ጠባቂዎች ጭፍጨፋ እና የሕክምና መመራመሪያ በመሆን የተገደሉት ይጠቀሳሉ።

በማጎሪያ ካምፑ አይሁዳውያን፣ ሮማውያን እና ጂፕሲዎችን ጨምሮ 200,000 ሰዎች ተይዘው ነበር።

የፍርድ ውሳኔው በተላለፈበት ቀን ጆሴፍ “ለምን በዚህ ኀጥአት እንደተወነጀልኩ አላውቅም። ከደሙ ንጹህ ነኝ” ማለታቸው ተዘግቧል።

በወቅቱ የማጎሪያ ካምፑ ጠባቂ ሳይሆኑ የግብርና ሠራተኛ እንደነበሩም ተከራክረዋል።

ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ኡዶ ሌችተርማን በበኩላቸው፣ ግለሰቡ እአአ ከ1942 ጀምሮ በካምፑ ውስጥ ለሦስት ዓመታት እንደሠሩ ማስረጃ እንደተገኘ ተናግረዋል።

“በሙያህ ያንን የጅምላ ጭፍጨፋ አግዘሀል” ሲሉም ዳኛው ተደምጠዋል።

የናዚ የማጎሪያ ካምፕ ጥበቃዎችን ለተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችና ግፎች ፍድር ቤት ማቆም የተቻለው ከ2011 ወዲህ ነው።

በወቅቱ የቀድሞው የኤስኤስ ጠባቂ የነበረ ጆን ደምጃንጁክ የተባለ ግለሰብ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ከዚህ ፍርድ በኋላ በሕይወት ያሉ የናዚ የቀድሞ ጥበቃ ሠራተኞችን መፈለግ ተጀምሯል።

ኦስከር ግሮኒንግ የተባሉ የ97 ዓመት ግለሰብና የቀድሞ የማጎሪያ ካምፕ የጥበቃ ሠራተኛ በሰሜን ጀርመን ለፍርድ ቀርበዋል።