ኡጋንዳዊው የመብት ተሟጋች እስር ቤት ውስጥ በፖሊስ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰበት ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኡጋንዳዊው የመብት ተሟጋች እስር ቤት ውስጥ ሳለ በፖሊስ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰበት ጠበቃው ተናገሩ።

የመብት ተሟጋቹ ባሳለፍነው ሳምንት ከታሰሩ የተቃውሞ ሰልፈኞች አንዱ ነው።

ከ90 በላይ ወጣቶች የታሠሩ ሲሆን፣ የተወሰኑት ሕዝብን አውከዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ወጣቶቹ በመዲናዋ ካምፓላ ሙስናን በመቃወም ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ከእስር ከተለቀቁት መካከል እስር ቤት ሳሉ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው የገለጹ አሉ።

ይህም ከፍተኛ ቁጣን አስነስቷል።

ፖሊስ የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።

ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ‘በእሳት መጫወት ነው’ ብለው ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም ባለፈው ማክሰኞ እና ሐሙስ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በኬንያ የታክስ ረቂቅ ሕግን በመቃወም ለሳምንታት በቀጠለው ተቃውሞ ተነሳስተው የኡጋንዳ ወጣቶችም አደባባይ ወጥተዋል።

በሙስና ስማቸው የተነሳው የኡጋንዳ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሥራቸውን እንዲለቁ ተቃዋሚዎቹ ጠይቀዋል። አፈ ጉባዔዋ ክሱን አስተባብለዋል።

የኡጋንዳ ፖሊስ ወጣቶቹን ብዙም ሳይርቁ አስቁሟቸዋል። ታዋቂ የቴሌቭዥን አቅራቢን ጨምሮ ወጣት የመብት ተሟጋቾች ታስረዋል።

የተወሰኑት ተቃዋሚዎች የተለያዩ ክሶች የቀረቡባቸው ሲሆን፣ ቁጥራቸው ያልታወቀ ተቃዋሚዎች አሁንም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ናቸው።

ጠበቃ ኤሮን ኪዛ እንዳሉት፣ በእስር ቤት ውስጥ የተለመደ ዓይነት ጥቃት ባይሆንም ደንበኛቸው በፖሊስ እስር ላይ ሳለ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶበታል።

ካምፓላ ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ “በፖሊስ ይዞታ ሳሉ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ጉዳይ ይመርመር። ተጠያቂነትም ይስፈን” ብሏል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ኪቱማ ሩሶክ ክሱን “መሠረተ ቢስ” እና “ሐሰተኛ” ብለው አጣጥለዋል።

ጠበቃው እንዳሉት፣ ፖሊሶች ከተቃዋሚዎች ጀርባ የውጭ አገራት ለጋሾች እንዳሉ ያምናሉ።

ኡጋንዳ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ላይ በጣም ጠንካራ ሕግ ከማውጣቷ ጋር በተያያዘ ለጋሾች ድጋፍ ማቋረጣቸው ይታወሳል።

ደንበኛው ወሲባዊ ጥቃት ሲደርስበት “ይገባሀል” መባሉን አክለው ተናግረዋል።

“በተቃዋሚዎቹና በውጭ አገር ለጋሾች መካከል ፖሊስ በግድ ትስስር ለመፍጠር እየሞከረ ነው። እንደ በቀል ነው የወሰዱት” ብለዋል።

ደንበኛቸው ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰበት የሚያሳዩ የሕክምና ማስረጃዎች እንዳሏቸውና ሲያገግም የመንግሥት አካላት ላይ ማስረጃውን ይዘው ክስ እንደሚመሠርቱ አክለዋል።

ሴቶችና ወንዶች ተቃዋሚዎች በፖሊስ ተይዘው ሳለ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተቃዋሚው ቦቢ ዋይን ተናግሯል።

“በአደባባይ መናገር የቻሉት ጥቂቱ ብቻ ናቸው። በይፋ ከተናገሩት የሚደርስባቸውን በመፍራት ለኛ የነገሩን ብዙ ናቸው” ብሏል።

ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ በኡጋንዳ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተጠየቀ ነው።

የወጣቶች ሚኒስትር ባላም ባሩጋራህ አቴኒ በኤክስ ገጻቸው “እውነት ከሆነ፣ ይህንን ድርጊት የፈጸማችሁ ሰዎች ፈጣሪ ይቅጣችሁ” ብለዋል።

ድርጊቱ ኢ-ሰብአዊ እንደሆነ ገልጸው፣ ፖሊስ ጉዳዩን እንዲመረምር ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ “በውጭ ኃይሎች የተደገፈ” ያሉትን ተቃውሞ ፖሊሶች በማስቆማቸው አመስግነዋል።

በፍርድ ቤት ስለ ተቃውሞዎቹ “መጥፎ ነገሮች ይፋ ይሆናሉ” ሲሉም አክለዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የታሰሩት ሰዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠይቋል።

“የኡጋንዳ መንግሥት ሰላማዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን ኃይል የመጠቀም ስልቱን አሁንም ፈጽሟል” ሲል መግለጫ አውጥቷል።