ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በታይላንድ በደረሰ የመኪና አደጋ ቢያንስ 20 ልጆች ሳይሞቱ አይቀርም ተባለ
ከታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ሕጻናት ተማሪዎችን ያሳፈረ አውቶብስ ላይ አደጋ ደርሶ በእሳት በመያያዙ ተማሪዎች እና መምህራን ላይ ጉዳት ደረሰ።
የአገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስትር 16 ተማሪዎች እና ሦስት መምህራን ከአደጋው መትረፋቸውን ቢገልጹም እስካሁን ድረስ 22 ተማሪዎች እና ሦስት መምህራን ያሉበት ሁኔታ ማወቅ አልተቻለም።
የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በአደጋው “ሞት እና ጉዳት” መከሰቱን የገለፁ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ግን ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ በእርግጠኝነት አልተገለጸም።
ከአደጋው በኋላ የወጡ ፎቶግራፎች አውቶብሱ በእሳት ሙሉ በሙሉ መውደሙን ያሳያሉ።
የታይላንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን፤ “መርማሪዎች በእሳቱ ነበልባል የተነሳ ወደ መኪናው መግባት አልቻሉም” ሲሉ ዘግበዋል።
ከአደጋ ከተረፉት 19 ሰዎች መካከል ስምንቱ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መላካቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ገልጿል።
አውቶብሱ ተማሪዎችን ከትምህርታዊ ጉብኝት ይዘው እየተመለሱ ከነበሩ ሦስት አውቶብሶች መካከል አንዱ ነበር።
የአገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሱሪያሄ፣ አውቶብሱ የሚንቀሳቀሰው “እጅግ አደገኛ በሆነ” የታመቀ የተፈጥሮ ጋዝ ነበር ብለዋል።
“እጅግ በጣም አሳዛኝ አደጋ ነው” ሲሉም ተማሪዎቹን አሳፍሮ የነበረው እና በእሳት የጋየው አውቶብስ ከሚገኝበት ስፍራ ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ መንገደኞች የሚያመላልሱ መኪኖች እንዲህ ዓይነት ነዳጅ እንዳይጠቀሙ የሚታገድበትን መፍትሄ ለማበጀት ይሠራል. . . ምንክያቱም በጣም አደገኛ ነው” ብለዋል።
የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው የአገሪቱ ሚኒስትሮች በአደጋው ስፍራ ተገኝተው እንዲጎበኙ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
“እንደ እናት ሕይወታቸውን ላጡት ሰዎች የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን መግለጽ እፈልጋለሁ” ብለዋል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር።
“መንግሥት የሕጻናቱን የሕክምና ወጪ እና ካሳ ይሸፍናል” ሲሉም አክለዋል።
በአደጋው ወቅት በስፍራው ተገኝተው ነፍስ የማዳን ሥራ ሲያከናውን የነበረውን ቡድን የመሩት ፒያላክ ቲንካዌ የሞቱት ሰዎችን ማንነት ለመለየት እስኪያስቸግር ድረስ በእሳቱ መቃጠላቸውን ገልጸዋል።
“የተወሰኑት ያገኘናቸው የአካል ክፍሎች በጣም በጣም ትንሽ ናቸው” ሲሉ በቦታው ለተገኙ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“የሕጻናቱ እርምጃ በመኪናው የኋላኛ ክፍል ማምለጥ ስለነበር በርካቶቹን አስከሬኖች ያገኘነው ከመኪናው የኋላ ክፍል ነው” ሲሉ አክለዋል።
አውቶብሱ ወደ ባንኮክ እየተጓዘ በነበረበት ወቅት ጎማው ፈንድቶ አደጋው እንደደረሰበት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ለአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
አውቶብሱን ሲያሽከረክር የነበረው ግለሰብ የአደጋውን መድረስ ተከትሎ ከአካባቢው የሸሸ ቢሆንም ባለሥልጣናት ግን አድነው እንደሚይዙት ገልጸዋል።
በአውቶብሱ ላይ የነበሩት ተማሪዎች ዕድሜ ስንት እንደሆነ እስካሁን ድረስ ይፋ ባይደረግም፣ ትምህርት ቤቱ ግን ዕድሜያቸው ከሦስት እስከ 15 ዓመት የሚሆኑ ሕጻናትን የሚያስተምር ነው።
ታይላንድ በመንገድ ደኅንነት አደገኛ ከሚባሉ የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፣ የተሽከርካሪ ብቃት ማነስ እና የመንገዶች ምቹ አለመሆን ተደማምረው ቢያንስ በዓመት 20 ሺህ አደጋዎች ይከሰታሉ ተብሏል።