የሩሲያ ኃይሎች ሲያፈገፈጉ ዩክሬን ቁልፍ ከተሞችን እየያዘች ነው  

ታትሟል

የዩክሬን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት መሳካቱን ተከትሎ የሩሲያ ኃይሎች ቁልፍ ከሆኑ የሃገሪቱ ምስራቃዊ ከተሞች ለቀው ወጥተዋል።

የዩክሬን ባለስልጣናት እንዳሉት ቅዳሜ ዕለት ወታደሮቻቸው ለሩሲያ ኃይሎች ወሳኝ አቅርቦት ማዕከል የሆነችውን ኩፒያንስክ ተቆጣጥረዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ወታደሮቹ "እንደገና ለመሰባሰብ” በአቅራቢያው አዚዩም አፈግፍገዋል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ አክሎም በዶኔትስክ ግንባር ላይ ያለውን "ጥረትን ለማጠናከር" ከሦስተኛ ቁልፍ ከተማ ባላክሊያ ወታደሮቹ ለቀው መውጣታቸውን አረጋግጧል።

የዩክሬን የጦር ግስጋሴ ሩሲያ በሚያዝያ ወር በኪዬቭ ዙሪያ ካሉ አካባቢዎች ከወጣች በኋላ የተገኘ በጣም ጠቃሚ ስኬት ይሆናል።

ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ቅዳሜ ዕለት የምሽት መግለጫቸው ዩክሬን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አዲስ የመልሶ ማጥቃት ከጀመረች በኋላ 2 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ከሩሲያ ነፃ አውጥታለች ብለዋል።

እንደመግለጫው ከሆነ ከዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆነው ባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥ እንደገና መያዙን የሚጠቁም ነው። ምክንያቱም ዘሌንስኪ ከዚህ በሁለት እጥፍ የሚሆነው ቦታ መያዙን የጠቆሙት ሐሙስ አመሻሽ ነበር።  

የሞስኮ ዋና ወታደራዊ ማዕከል ስለነበረች ሩሲያ ከኢዚዩም ለቃ መውጣቷ ትልቅ አንድምታ አለው።

“በሦስት ቀን ዘመቻ የአዚዩም-ባላክሊያ ወታደሮችን ወደ ዶኔትስክ ​​ህዝባዊ ሪፐብሊክ ግዛት የማዛወር እና የማደራጀት ሥራ ተከናውኗል" ሲል የሩሲያ መግለጫ ገልጿል።

"በሩሲያ ወታደሮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል በጠላት ላይ ኃይለኛ የእሳት ሽንፈት ተፈጽሟል" ብሏል። 

ብዙም ሳይቆይ በሩሲያ የሚተዳደረው የካርኪቭ ክልል ዋና አስተዳዳሪ "ሕይወት ለማዳን" ሲባል ነዋሪዎች ወደ ሩሲያ ክልል እንዲያቀኑ ሐሳብ አቅርበዋል ሲል በሩሲያ መንግሥት የሚተዳደረው ታስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በሩሲያ ሥርየሚገኘው የቤልጎሮድ ክልል ገዥ ድንበሩን ለማቋረጥ ለሚሰለፉ ሰዎች ጊዜያዊ የምግብ አቅርቦት፣ ማሞቂያ እና የህክምና እርዳታ እንደሚደረግ ተናግረዋል ።

ግስጋሴው የዩክሬን ጦር በራሺያ እጅ የሚገኙ ግዛቶችን መልሶ የመውሰድ አቅም እንዳለላት የሚያሳይ ምልክት ተደርጎ ተወስዷል። ይህም ወሳኝ ሲሆን ኪዬቭ በከባድ ጫና ውስጥ የወደቁትን ምዕራባውያን አጋሮቿን ወታደራዊ ድጋፍ ጠይቃለች።

የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲሚትሮ ኩሌባ እንደተናገሩት አሁን የታዩት ውጤቶች የሩስያ ጦርን ማሸነፍ መቻላቸውን እና በምዕራባውያን የጦር መሳሪያዎች ጦርነቱን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ባለስልጣናት ዩክሬን 50 ኪ.ሜያህል ቀደም ሲል በሩሲያ ወደተያዙ ግዛቶች መግባቷን ተናግረዋል ።

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር "የሩሲያ ወታደሮች ሳይገረሙ አልቀረም።የዩክሬን ኃይሎች ብዙ ከተሞችን ይዘዋል ወይም ከበዋል” ብሏል። 

ዩክሬን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻውን በምስራቅ የጀመረች ሲሆን ዓለም አቀፉ ትኩረት በደቡባዊ ኬርሰን ከተማ አቅራቢያ በሚጠበቀው ግስጋሴ ላይ ያተኮረ ነበር።

ተንታኞች እንደሚያምኑት ከሆነ ሩሲያ ከተማዋን ለመከላከል በጣም ልምድ ያካበቱ ወታደሮቿን ልካለች።

ከምስራቅ በተጨማሪ ዩክሬን በደቡባዊ አቅጣጫም ድል እያስገኘች ነው ሲሉ አንድ ባለስልጣን ተናግረዋል።

የዩክሬን ጦር ደቡባዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ናታሊያ ጉሜንዩክ በበኩላቸው በግንባሩ “ከሁለት እስከ በርካታ ደርዘን የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች” መጓዛቸውን ተናግረዋል።

በደቡባዊ ግንባር የሚፋለመው የሩስያ ጦር ወደ መከላከል  ገብቷል እየተባለ ሲሆን የዩክሬን ወታደሮች ጥቃቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ መከላከል ገጥሟቸዋል።

ቅዳሜ ዕለት ካርኪቭ በሩሲያ ሮኬቶች በመምታቷ አንድ ሰው ተገድሎ በርካታ ቤቶች ተጎድተዋል ሲሉ የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።