ሰዎች በረሃብ እየሞቱባት ነው የተባለችው ሰሜን ኮሪያ

ሰሜን ኮሪያ
ታትሟል

በሰሜን ኮሪያ በገጠመው የምግብ እጥረት ሳቢያ ጎረቤቶቻቸው በረሃብ መሞታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከዓለም በተገለለችው ሰሜን ኮሪያ የሚኖሩና በተለይ ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡ ነዋሪዎች እንደተናገሩት በረሃብ ጎረቤቶቻቸው እየሞቱ ነው።

ሁኔታው ከ1990ዎቹ የከፋ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በ2020 የአገሪቱ መንግሥት ድንበሮች ዘግቷል። መሠረታዊ አቅርቦት እየገባ አይደለም።

ነዋሪዎች ላይ ቁጥጥር እንደበረታም ይናገራሉ።

የአገሪቱ መንግሥት ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ምንግዜም ለዜጎች ቅድሚያ ይሰጣል።

ቢቢሲ በአገሪቱ ሦስት ሰዎችን በምሥጢር አነጋግሯል። ከአገሪቱ ነዋሪዎች መስማት እምብዛም አልተለመደም።

ድንበር ከተዘጋ በኋላ በረሃብ እንሞታለን ወይም ሕግ ጥሳችኋላ ተብለን እንገደላለን ብለው ይሰጋሉ።

“ከፍተኛ ቀውስ እየተከሰተ ነው” የሚለው ‘ሊበርቲ ኢን ኖርዝ ኮርያ’ የተባለ ተቋም ሠራተኛው ሶከል ፓርክ ነው።

ተቋሙ ሰዎች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ያመቻቻል።

በመዲናዋ ፒዮንግያንግ የምትኖር አንዲት ሴት እንዳለችው ሦስት የቤተሰብ አባላት በረሃብ ሞተዋል።

“ውሃ ልንሰጣቸው በር አንኳኳን። ማንም አልከፈተልንም” ስትል ትናገራለች።

ባለሥልጣኖች ወደ ቤቱ ሲገቡ አስክሬናቸውን አገኙ።

ከቻይና ጋር በሚያዋስነው ድንበር አቅራቢያ የግንባታ ሠራተኛ የሆነና ስሙን የማንጠቅሰው ግለሰብ እንዳለው የምግብ እጥረት ስላለ በሚኖርበት መንደር አምስት ሰዎች ሞተዋል።

“በኮቪድ እንዳልሞት ፈርቼ ነበር። አሁን የምፈራው በረሃብ እንዳልሞት ነው” ይላል።

አገሪቱ ለ26 ሚሊዮን ዜጎቿ የሚበቃ ምግብ ማምረት አልቻለችም።

ድንበሩ ሲዘጋ ከቻይና እህል፣ ማዳበሪያ እና የግብርና ማሽን ማስገባት ቆሟል።

ድንበሩን ለማለፍ የሚሞክር ሰው ይተኮስበታል። ስለዚህ ሰዎች ምግብ ማስገባት አይችሉም።

አብዛኞቹ ሰሜን ኮሪያውያን በዚህ መንገድ የሚገባን እሀል ከኢ መደበኛ ገበያ ነው የሚገዙት።

ምግብ እየገባ አለመሆኑ ግን እጥረቱን አባብሶታል።

አንድ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነጋዴ እንዳሉት ገበያው ላይ ካለው እህል ሲሶው የሚገባው ከቻይና ነበር።

አሁን ግን “ምንም የለም” ይላሉ።

እንደማንኛውም የምግብ ነጋዴ ገቢያቸው ቀንሷል። የተራቡ ሰዎች ቤታቸው እየሄዱ ምግብ ይጠይቋቸዋል።

ሌላዋ ነዋሪ እንደነገረችን ራሳቸውን ያጠፉም ሰዎች አሉ።

ወደ ተራራማ ቦታ ለመሞት የሄዱ እንዳሉም ሰምታለች። እነዚህ ሰዎች ኑሮን መግፋት ተስኗቸዋል።

እሷም ልጆቿን መመገብ አልቻለችም። ለሁለት ቀናት ሳትበላ ቆይታ ባሸለበችበት ልትሞት ተቃርባ ነበር።

በ1990 በሰሜን ኮሪያ አስከፊ ነሃብ ተከስቶ ነበር። ወደ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል።

አሁንም ይሄ ይከሰታል ተብሎ ተሰግቷል።

የምጣኔ ሀብታ ባለሙያው ፒተር ዋርድ “መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል። አሳሳቢ ነው” ይላል።

ወደ አገር አቀፍ ረሃብና ወደ ማኅበረሰባዊ ውድቀት እያመሩ ባይሆንም ነገሮች አሳሳቢ መሆናቸውን ያስረግጣል።

የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚመዘግበው ተቋም ኤንኬዲቢ ዳይሬክተር ሃና ሶንግ እንደምትለው ባለፈው 10 እና 15 ዓመት ረሃብ አልታየም። የኋላ ታሪካቸው ግን አስከፊ ነበር።

የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሳይቀሩ ስለ ነገሩ አሳሳቢነት ገልጸዋል።

“የምግብ ቀውስ” ተፈጥሯል ብለው አምነዋል። የግብርና ምርትን ለማሳደግ እየተሞከረ ነው።

ሰሜን ኮሪያ

ሆኖም ግን መሪው ለኒውክሌር ግንባታ ቅድሚያ ሲሰጡ ይስተዋላል።

አምና 63 ባለስቲክ ሚሳዔል ሞክረዋል።

ሙከራው ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስወጣል። ይህም ከአገሪቱ ዓመታዊ ዕድገት የበለጠ ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት መንግሥት የሕዝቡ ሕይወት ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር መበርታቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቅጣት በመጣልና ሕግ በማጥበቅ ቁጥጥሩ ጨምሯል።

ከወረርሽኙ በፊት በቀን አንድ ሺህ ሰዎች ከአገሪቱ ይወጡ ነበር።

ያሉ ወንዝን አልፈው ወደ ቻይና ይገባሉ።

ነጋዴው እንደነገሩን አሁን ከአገሪቱ ማምለጥም አይቻልም።

“አሁን ወደ ወንዙ የተጠጋ ሰው እንኳን ከባድ ቅጣት ስለሚጣልበት ማንም ደፍሮ አይሞክረውም” ይላሉ።

የግንባታ ሠራተኛው እንደሚለው የጓደኛው ልጅ ብዙ ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት በድብቅ ሲተገበር አይቷል።

ለመሸሽ የሞከሩ ከሦስት እስከ አራት የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።

“እያንዳንዱ ቀን እየተባባሰ ነው። አንድ ስህተት ብንሠራ እንገደላለን” ይላል።

ድንበሩ ከተዘጋ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኗል።

መውጣትም መግባትም አይቻልም።

የውጭ አገር ዜጎች ለቀው ወጥተዋል።

ምሥጢራዊና ድብቅ አገር ነው። ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሦስት ሰዎች ሕይወታቸውን ለአደጋ ሰጥተው ነው ቃላቸውን የሰጡት።

ከመንግሥት ምላሽ ስንጠይቅ “በከባድ ጊዜ ውስጥም መንግሥት ለዜጎቹ ደኅንነት ቅድሚያ ይሰጣል” የሚል ምላሽ አግኝተናል።

በለንደን የሚገኙት የሰሜን ኮሪያ ወኪል በፈታኝ ጊዜም ቢሆን ለዜጎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከነዋሪዎች ያገኘው ምስክርነት “ውሸት” እንደሆነና “ከሰሜን ኮሪያ ጠላቶች የተፈጠረ” እንደሆነም ገልጸዋል።

የመብት ተሟጋቾች ግን ሰቆቃውን ይገልጻሉ።

ሰሜን ኮሪያ

“ምግብ እጥረት አሳሳቢ ሆኗል። የሰዎች መብትም እየተረገጠ ነው። ከአገር መውጣትም አይቻልም” ይላሉ።

የፒዮንግያግ ነዋሪ የደኅንነት ቁጥጥርና ቅጣት እንደበረታ ትናገራለች።

ሰዎችም እርስ በእርስ መተማመን አቅቷቸዋል።

የውጭ አገር ፊልምና ሙዚቃ መስማት በሚከለክለው አዲስ ሕግ መሠረት ፖሊስ ቃሏን ለመቀበል ወስዷት ነበር።

በዚህ ሕግ መሠረት የደቡብ ኮሪያ ይዘት ያላቸው መዝናኛዎች ያስተላለፈ ሰው ይቀጣል።

የቀድሞ የደቡብ ኮሪያ ዲፕሎማትና ወደ ሰሜን ኮሪያ የከዱት ርዩ ሁዋን ው አገዛዙ ምን ያህል እየከፋ እንደመጣ ሲያዩ ይሰጋሉ።

“ኪም ጆንግ ኡን ሰዎች ያሉበትን ሁኔታና የሰሜን ኮሪያ ሃብታሞች እንዴት እንደሚኖሩ ካወቁ እንደሚጠሉናት እንደሚነሱበት ያውቃል። ስለዚህም ይፈራል” ይላሉ።

“ከኮቪድ በፊት ሰዎች መሪውን በተሻለ ሁኔታ ያዩት ነበር። አሁን ግን ጥላቸው ጨምሯል” ሲሉም ያክላሉ።