ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል በሶሪያ ባሉ በርካታ ዒላማዎች ላይ የሮኬት ጥቃት ፈጸመች
እስራኤል በምትቆጣጠረው ግዛት የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በሶሪያ በርካታ ወታደራዊ ኢላማዎችን በሮኬቶች መምታቷን የአገሪቱ ጦር አስታወቀ።
ስድስት ሮኬቶች ወደ ጎላን ተራሮች መተኮሳቸውን ተከትሎ እስራኤል የሶሪያ ጦር ሰፈርን እና ሮኬቶችን ለመምታት መድፍ እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተጠቅማለች።
ባለሥልጣናቱ ሦስት ሮኬቶች ወደ እስራኤል ግዛት መግባታቸውን ተናግረዋል። ሁለቱ ክፍት ቦታዎች ላይ ሲወድቁ ሦስተኛው ተመትቶ ወድቋል።
የሶሪያ መከላከያ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መልዕክት ጥቃቱን አረጋግጧል።
የመከላከያ ባለስልጣናት የአየር መከላከያዎች ለጥቃቱ ምላሽ መስጠታቸውን እና የተወሰኑ ሚሳኤሎችን በተሳካ ሁኔታ ማምከኑን ተናግረዋል። በጥቃቱ ከደረሰው የንብረት ጉዳት በስተቀር በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶሪያ መንግስት መገናኛ ብዙሃን በርዕሰ መዲናዋ ደማስቆ አቅራቢያ ፍንዳታ መድረሱን ዘግቧል።
ቀደም ሲል ከሶሪያ ግዛት ሮኬቶች በመተኮሳቸው በጎላን ተራሮች የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ የተደወለ ቢሆንም ምንም አይነት ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት አልደረሰም።
የሊባኖስ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት በኢራን የሚደገፈውና የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ታጠቂ ክንፍ የሆነው የአል ቁድስ ብርጌድ በጥቃቶቹ እጁ እንዳለበት ተናግሯል።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት እሑድ ዕለት በሰጠው መግለጫ “በግዛቷ ውስጥ ለሚፈጠሩት እንቅስቃሴዎች ሁሉ ተጠያቂ የሚሆነው የሶሪያን መንግስት ነው" ያለ ሲሆን "የእስራኤልን ሉዓላዊነት ለመድፈር የሚደረጉ ሙከራዎችን አንፈቅድም” ብሏል።
እስራኤል በ1967 በተካሄደው በስድስቱ ቀናት ጦርነት ወቅት 1200 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሰፋውን እና በሶሪያ ስር የነበረውን የጎላን ተራሮችን ተቆጣጥራ ቆይታ በ1981 የግዛቷ አካል አድርጋዋለች።
ጥቃቶቹ የደረሱት በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው። አርብ ዕለት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን በሆነው ሃማስ ይዞታ የሆኑ በርካታ ኢላማዎችን መታለች። ሐሙስ ዕለት ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ለተተኮሱት 34 ሮኬቶች ቡድኑን ተጠያቂ አድርጋለች።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ደግሞ በምስራቅ እየሩሳሌም በሚገኘው አል-አቅሳ መስጊድ ውስጥ መሆናቸው ከእስራኤል ፖሊስ ጋር ተጨማሪ ግጭት እንዳይፈጠር ስጋት ፈጥሯል።
ፖሊሶች መስጂዱን ከወረሩ አስከፊ መዘዝ እንደሚያስከትል ዮርዳኖስ አስጠንቅቃለች።