እስራኤል በሐማስ ከታገቱ ዜጎቿ መካከል ተጨማሪ አራት መሞታቸውን አረጋገጠች

ታትሟል

ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ከፈጸመው ጥቃት ጋር ቴኣይዞ ከታገቱ እስራኤላውን መካከል ተጨማሪ አራት ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ሠራዊት አረጋገጠ።

እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ኻን ዩኒስ በተባለ ስፍራ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ እያከነወነች በነበረበት ጊዜ አራቱ ታጋቾች በጋራ መገደላቸውን የገለጸው ጦሩ አስክሬናቸው እስካሁን በታጣቂዎቹ እጅ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

የእስራኤል እና የብሪታንያ ጥምር ዜግነት ያላቸው ታጋቾቹ የ51፣ የ79፣ የ80 እና የ85 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ እንደነበሩ ተነግሯል።

የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሀጋሪ ጦሩ በቅርቡ በስለላ ክፍሉ አማካኝነት ባደረገው አሰሳ ታጋቾቹ መገደላቸው መረጋገጡን ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም የእስራል ጦር ሐማስ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ እየካሄደ በነበረበት ጊዜ ታጋቾቹ መገደላቸውን አስታውቀዋል።

አሁን ተገድለዋል ከተባሉት ታጋቾች አንዱ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት መሞቱን ባለፈው ወር ሐማስ ገልጾ ነበር። የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጉዳዩን እየመረመረ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ እስካሁን ስለሞቱ የሰጠውው ማረጋገጫ የለም።

የተቀሩትን ሦስት ታጋቾች የሚያሳይ ቪዲዮ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ሐማስ ለቆ ነበር።

አራቱም ታጋቾች መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ ታጣቂዎች ከጋዛ ሰርጥ አቅራቢያ ከሚገኘው የእስራኤል ግዛት ታግተው የተወሰዱ ናቸው።

ከሐማስ ጥቃት በኋላ የታጋቾች እና የጠፉ ሰዎች ቤተሰቦች የመሠረቱት ጥምረት ጉዳዩን አስመለክቶ በሰጠው መግለጫ፣ የአራቱ ታጋቾች ሞት እያንዳንዱ መሪ ጥልቀት ያለው ክትትል እንዲያደርግ ሊያነቃው ይግባዋል ብለዋል።

ጨምረውም አራቱ ሰዎች በሕይወት እያሉ መታገታቸውን እና አንዳንዶቹ በተደረገ ስምምነት ከተለቀቁት ታጋቾች ጋር እንደነበሩ አስታውሰው የተቀሩትም በሕይወት ሊመለሱ ይገባል ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ዴቪድ ካሜሮን በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ከታጋቾቹ መከካከል አንዱ በሆነው ናዳቫ ፖፔልዌልስ የሞት ዜና “እጅግ ማዘናቸውን” ገልጸው፤ ለወዳጆቹ እና ቤተሰቦቹም መጽናናትን ተመኝተዋል።

ናዳቫ ፖፔልዌልስ አሁን ከተለቀቁት እናቱ ጋር ነበር ከመኖሪያ ቤቱ በሐማስ ታጣቂዎች የታገተው። ወንድሙ ሮያ በጥቃቱ ሕይወቱን አጥቷል።

የእስራኤል ባለሥልጠናት እንደሚገልጹት ከሆነ ከወራት በፊት ሐማስ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎችን ደግሞ ታግተዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ለአንድ ሳምንት በቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት 105 ሲቪል ሰዎችን ለቋል። ወደ 120 የሚሆኑት ደግሞ እስካሁን በታጣቂዎቹ እጅ ይገኛሉ። የእስራኤል ባለሥልጣናት አብዛኞቹ ታጋቾች ሟተዋል ተብሎ እንደሚታመን ገልጸዋል።

እስራኤል ሐማስ ለፈጸመባት ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እና ቡድኑን ለማጥፋት ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈት ወራት ተቆጥሯል።

ባለፉት 8 ወራት በነበረው ጥቃት 36 ሺህ 470 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር የሚገኘው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።