የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት፡ ማንቸስተር፣ አርሰናል፣ ሊቨርፑል. . . ድል ይቀናቸው ይሆን?

ማንቸስተር ዩናይትድ ካለፉት አምስት የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች በአራቱ ተሸንፏል። ሰኞ ዕለት የአውሮፓውያኑ 2024 የመጨረሻ ጨዋታዎችን ከኒውካስል ሲያደርግ ድል ይቀናው ይሆን?
የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን "በዚህ ጨዋታ ምን እንደሚፈጠር ለማወቅ ከባድ አይሆንም" ይላል።
"ኒውካስል የሚገርም ብቃት ላይ ናቸው። የማንቸስተር ዩናይትድ ጉዳይ እጅግ እያሳሰበኝ ነው። አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ገና ከአሁኑ ፈገግታቸው ጠፍቷል።"
ሱተን እሑድ፣ ሰኞ እና ረቡዕ የሚደረጉ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ግምት እንዲህ አስቀምጧል።

እሑድ
ሌስተር ከሲቲ
ማንቸስተር ሲቲ በጣም አስከፊ የሚባል ጊዜ እያሳለፉ ነው። የፈለገ ውጤት ቢርቃቸውም እንደ ሌስተር ግን አይሆንም።
ሌስተር ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ቢያንስ በጨዋታ ሶስት ጎሎች አስተናግደዋል። ምናልባት የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ፔፕ ጉዋርዲዮላ አሁን የሚያስፈልገው እንደ ሌስተር ያለ ተጋጣሚ ነው።
የሌስተሩ አሰልጣኝ ሩድ ቫን ኒስትልሮይ ከባድ ሥራ ይጠብቀዋል። ለሌስተር ዋናው ዓላማ መሆን ያለበት በሊጉ መቆየት ነው።
ሲቲ በዚህ ጨዋታ ነጥብ ይጥላል ብዬ አልጠብቅም። ነገር ግን ጄሚ ቫርዲ ከተሰለፈ ጎል ሊያስቆጥሩ ይችላሉ።
ግምት፡ 1 - 2
ፓላስ ከሳውዝአምፕተን
ፓላስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነቃቃት እያሳዩ ይመስላሉ። ባለፈው ሳምንት ከቦርንመዝ አቻ ሲወጡ ይህን ተመልክተናል።
አዲስ አሰልጣኝ የሾመው ሳውዝአምፕተንም ቢሆን የመጀመሪያው ጨዋታውን ቢሸነፍም ተጋድሎ አሳይቷል።
ሳውዝአምፕተኞች አጨዋወታቸውን የቀየሩ ይመስላሉ። ኳስ ይዞ ከመጫወት ይልቅ በረዥም ኳስ ወደፊት መገስገስን መርጠዋል።
ይህ ጨዋታ ጥሩ ፍልሚያ ይታይበታል። ቀልቤ የሚነገርኝ ግን ፓላስ እንደሚያሸንፍ ነው።
ግምት፡ 1 - 0
ኤቨርተን ከፎረስት
ኖቲንግሀም ፎሬስት እየገሰገሰ ነው። ኤቨርተን ደግሞ ከአርሰናል፣ ቼልሲ እና ማንቸስቲር ሲቲ ባደረገው ጨዋታ አቻ ወጥቷል። እኔ በሶስቱም ጨዋታዎች ይሸነፋል ብዬ ነበር የገመትኩት።
ፎረስት ባለፈው ጨዋታቸው በኳስ ቁጥጥር ቢበለጡም ቶተንሀምን መርታት ችለዋል።
በዚህኛው ጨዋታ የሾን ዳይች ኤቨርተን የፎረስትን የፊት መስመር እንደሚቋቋም አምናለሁ።
ግምት፡ 1 - 1
ፉልሀም ከቦርንመዝ
ፉልሀም በገና ማግስት ጨዋታ ቼልሲን በስታንፈርድ ብሪጅ መርታት ችሏል። በስተመጨረሻው ደቂቃ ባስቆጠሯት ጎል ቼልሲን የረቱት ፉልሀሞች ውጤቱ ይገባቸዋል።
ቦርንመዝም እንዲሁ ጥሩ አቋም ላይ ነው። ነገር ግን በሜዳው ባደረጋቸው ባለፉት ሁለት ጨዋታ አቻ በመውጣት ግምቴን አበላሽቶታል።
ይህ ጨዋታ ለመገመት ከባድ ነው። ነገር ግን ውስጤ ወደ ፉልሀም አድልቷል።
ግምት፡ 2 - 1
ቶተንሀም ከዎልቭስ
ቶተንሀም ባለፈው ጨዋታ በፎረስት ተረትቷል። ምንም እንኳ አንጅ ፖስቴኮግሉ አጨዋወታቸው የማይጠገብ ቢሆንም ውጤት ማምጣት ግን አልቻሉም።
በአሁኑ ወቅት የተከላካይ መስመራቸው ሳስቷል። ይህኛውም ጨዋታ ቀላል ይሆናል የሚል ግምት የለኝም።
ዎልቭስ በአዲሱ አሰልጣኝ ቪቶር ፔሬራ መሪነት ሁለት ጨዋታዎች አሸንፈዋል። በሁለቱም ጨዋታዎች ምንም ጎል አልተቆጠረባቸውም።
ቢሆንም በዚህ ጨዋታ ቶተንሀም ያሸንፋል የሚል ግምት አለኝ።
ግምት፡ 2 - 1

ዌስት ሀም ከሊቨርፑል
ሊቨርፑልን የሚያቆመው ኃይል ይኖር ይሆን? ዌስት ሀም ይህ የሚቻለው አይመስለኝም።
ምንም እንኳ ዌስት ሀም በደረጃ ሰንጠረዡ ከዩናይትድ እና ስፐርስ በላይ ቢሆኑም የወትሮው ጥንካሬያቸው አይታየኝም።
ሊቨርፑል ተጨዋቾችን እየቀያየሩ ማሰለፍ ጀምረዋል። የአርን ስሎት ቡድን ግስጋሴው የሚቆም አይመስልም።
በዌስት ሀም ሜዳ የሚደረገው ጨዋታ በሊቨርፑል የበላይነት እንደሚጠናቀቅ እገምታለሁ።
ግምት፡ 0 - 2
ሰኞ
ቪላ ከብራይተን
ሁለቱም ቡድኖች ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ አቋማቸው እየወረደ መጥቷል። ይህ ደግሞ የግምት ሥራዬን ከባድ ያደርገዋል።
ብራይተን ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድም ድል አልቀናቸውም። ነገር ግን ሁለት ጊዜ ብቻ ነው የተሸነፉት።
የአስተን ቪላው ጆን ዱራን በቅጣት ምክንያት በዚህ ጨዋታ ባይሰለፍም ድል ይቀናቸዋል የሚል ግምት አለኝ።
ኦሊ ዋትኪንስ ለቪላ ጎል እንደሚያስቆጥር እገምታለሁ።
ግምት፡ 2 - 1
ኢፕስዊች ከቼልሲ
ቼልሲ በገና ሰሞን ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። ከኤቨርተን ያለምንም ጎል አቻ ተለያይቶ በፉልሀም ደግሞ ተሸንፏል።
የሰማያዊዎቹ አሰልጣኝ ለዋንጫ ፉክክር አልበቃንም ያሉት እውን ሳይሆን አይቀርም።
ነገር ግን በዚህ ጨዋታ ወደ ድል እንደሚመለሱ አምናለሁ። ኢፕስዊች አርብ ምሽት ከአርሰናል ጋር ተጋድሎ ቢያሳዩም 1 ለምንም ተረትተዋል።
ይህን ጨዋታ ቼልሲ ያሸንፋል የሚል ግምት ቢኖረኝም ኢፕስዊች ግን በቀላሉ ይረታል አልልም።
ግምት፡ 0 - 2

ዩናይትድ ከኒውካስል
ኒውካስል ባለፉት ሳምንታት ወደ ቀደመ አቋማቸው መመለሳቸውን አሳይተዋል። በኦልድ ትራፈርድ ዩናይትድን ከረቱ በአራት ጨዋታዎ ድል ቀናቸው ማለት ነው።
በተቃራኒው ዩናይትድ ውጤቱ ላሽቋል። ዩናይትድ ነጥብ ይጥላል ብዬ ስገምት ደጋፊዎች በማኅበራዊ ሚድያ ጠምደው ይይዙኛል።
አዲሱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ለዚህ ተጠያቂ አይሆንም። ምክንያቱም የራሱን ተጫዋቾች አምጥቶ ስናየው ነው ልንፈርድ የምንችለው።
ዩናይትድ ከኒውካስል ጋር በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ ያሸንፋል የሚል ግምት የለኝም።
ግምት፡ 1 - 2
ረቡዕ

ብሬንትፈርድ ከአርሰናል
የአርሰናሉ ቡካዮ ሳካ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ይርቃል። ይህ ለመድፈኞቹ አሳሳቢ ዜና ነው።
ብሬንትፈርድ በሜዳው እጅግ ፈታኝ ቡድን ነው። በተለይ በያዝነው የውድድር ዘመን በሜዳቸው የሚቻሉ አይደሉም።
ቢሆንም አርሰናል ይህን ጨዋታ በጠባብ ውጤት ሊረታ እንደሚችል እገምታለሁ። አርሰናል ይህን ጨዋታ በመርታት ወደ ሊቨርፑል ይጠጋል ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 0 - 1












