ከማራዶና ሞት ጋር በተያያዘ የህክምና ባለሙያዎች ለፍርድ ሊቀርቡ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስመ ጥር ከሆነው የአርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ዲያጎ ማራዶና ሞት ጋር በተያያዘ ስምንት የህክምና ባለሙያዎች በቸልተኝነት ተወንጅለው ለፍርድ ሊቀርቡ ነው።
የማራዶና ህክምና “ጉድለቶች እና ግድፈቶች” የታየበት መሆኑን መርማሪ የህክምና ቡድን ማረጋገጡን ተከትሎ ጉዳዩ በግድያ ወንጀል በችሎት እንዲታይ አርጀንቲናዊው ዳኛ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ታዋቂው እግር ኳስ ተጫዋች ማራዶና በ60 አመቱ በልብ ህመም ህይወቱ ያለፈው በመዲናዋ ቦነስ አይረስ በአውሮፓውያኑ 2020 ነው።
በሞተበት ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ የአንጎል ደም መርጋት ቀዶ ህክምና አድርጎ ቤቱ እያገገመ ነበር።
ማራዶና ከሞተ ጥቂት ቀናት በኋላ የአርጀንቲና አቃብያነ ህግ በህክምናው ውስጥ በተሳተፉ ዶክተሮች እና ነርሶች ላይ ምርመራ ከፈቱ።
በአውሮፓውያኑ ባለፈው አመት የአሟሟቱን ሁኔታ ለመመርመር የተቋቋመው 20 ባለሙያዎችን ያቀፈው ቡድን ማራዶናን ያከሙት የህክምና ባለሙያዎች "ተገቢ ያልሆነ፣ በግድየለሽነት የተሞሉ ነበሩ እንዲሁም ጉድለቶችም ታይተውባቸዋል የሚል ማጠቃለያ ላይ ደርሰዋል።
እግር ኳስ ተጫዋቹ በተገቢው የህክምና ተቋም ውስጥ በቂ ህክምና ቢደረግለት “የተሻለ የመትረፍ እድል ይኖረው ነበር” የሚል ድምዳሜም ላይ ፍርድ ቤቱ ደርሷል።
ክስ ከሚመሰረትባቸው መካከል የማራዶና የነርቭ ቀዶ ህክምና ባለሙያ እና የግል ዶክተር ሊዮፖልዶ ሉክ ፣ የሥነ አእምሮ ሐኪም እና የሥነ ልቦና ባለሙያ ፣ ሁለት ዶክተሮች ፣ ሁለት ነርሶች እና ኃላፊያቸው ይገኙበታል።
ሁሉም የህክምና ባለሙያዎች በማራዶና ሞት ላይ ቸልተኝነት አላሳየንም ሲሉ ክደዋል።
ስምንቱም የህክምና ባለሙያዎች ሰውን ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል በማወቅ በቸልተኝነት በተፈጸመ የግድያ ወንጀል ክስ ነው ፍርድ ቤት የሚቀርቡት።
በአርጀንቲና የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት ወንጀሉ ከስምንት እስከ 25 አመት እስራት ያስቀጣል። የፍርድ ሂደቱ የሚጀመርበት ቀን ገና አልተቆረጠም።












