አሜሪካ ለሕንድ የ4 ቢሊየን ዶላር ድሮን ሽያጭን አጸደቀች

አሜሪካ ሰራሽ ድሮን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የአሜሪካ የውጭ መሥሪያ ቤት አራት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ 31 ወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን)፣ ሚሳኤሎች እና ሌሎች ወታደራዊ ቁሶች ለሕንድ በሽያጭ እንዲተላለፉ አጸደቀ።

ኤምኪው-9ቢ ፕሪዴተር የተባለው ድሮን ለሕንድ በሽያጭ እንደሚተላለፍ ይፋ የተደረገው የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ባለፈው ዓመት ሰኔ በአሜሪካ ጉብኝት ባደረጉ ወቅት ነበር።

ይሁን እንጂ ኅዳር 2016 ዓ.ም. በአሜሪካ ምድር የሕንድ ዝርያ ባለው ግለሰብ ላይ ግድያ ለመፈጸም የሕንድ መንግሥት አሲሯል መባሉን ተከትሎ ምርመራ እንዲደረግ ከተወሰ በኋላ የሽያጭ ስምምነቱ እንዲዘገይ ተደርጎ ነበር።

ስምምነቱ በኮንግረሱ ከጸደቀ በኋላ የጦር መሳሪዎቹ ለሕንድ በሽያጭ ይተላለፋሉ ተብሏል።

ይህ ስምምነት 31 ኤምኪው-9ቢ ስካይጋርዲያን ድሮኖች፣ 170 ኤጂኤም-114አር ሄልፋየር ሚሳኤል እና የተለያዩ ዓይነት ቦምቦች፣ የግንኙነት እና የስለላ መሳሪዎችን እንደሚያካትት የአሜሪካ መከላከያ መሥረያቤት ፔንታገን አስታውቋል።

የሕንድ መንግሥት ተሳታፊ ሳሆን አይቀርበትም የተባለውን የግድያ ሴራን ሲመረምሩ የነበሩት የሴኔት ኮሚቴ አባሉ ሴናተር ቤን ካርዲን፣ የአሜሪካ መንግሥት ጉዳዩ ላይ ዝርዝር ምርመራ ለማድረግ ከተስማማ በኋላ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነቱ ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ እንዲነሳ መስማማታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የባይደን አስተዳደር ምርመራ አድርጎ ተጠያቂነትን እንደሚያረጋግጥ ተስማምቷል ያሉት ሴናተር ካርዲን፤ መሰል እንቅስቃሴዎች የሕንድ መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት ዋሽንግተን አሜሪካዊ ዜግነት ያለው እና ከሕንድ ተገንጥላ ካሃሊስታን የተባለች ሉዓላዊት አገር ለመመሥረት የሚንቀሳቅን ሕንዳዊ የዘር ግንድ ያለውን ግለሰብ አሜሪካ ምድር ላይ ለመግደል ዴልሂ አሲራለች ብላ ነበር።

የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን የአገሪቱ መንግሥት በጉዳዩ ምንም ተሳትፎ እንደሌለው ገልጿል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ጨምሮም ከአሜሪካ ዘንድ የቀረበውን ክስ እና የደኅንነት ስጋት የሚያጣራ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ያሉበት ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል።

ሐሙስ ዕለት ፔንታገን ወታደራዊ ቁሶቹ ለሕንድ በሽያጭ መተላለፋቸው የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ከመደገፉ በላይ የአሜሪካ-ሕንድ ስትራቴጂካዊ ግንኙነትን ያጠናክራል ብሏል።